Thursday, 19 December 2013

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ሆነው ተሾሙ

አስቸኳይ ስብሰባውን ከትናንት ምሽት ጀምሮ በባህር ዳር ያካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ርእሰ መስተዳድር ሾሟል። ምክር ቤት ለስምንት ዓመት ተኩል ክልሉን ያገለገሉት አቶ አያሌው ጎበዜን በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተክቷል። አቶ ገዱ ክልሉን በምክትል ርእሰ መስተዳድርነትና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ለምክር ቤቱ የስንብት ንግግር ያቀረቡት አቶ አያሌው ጎበዜ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። አቶ አያሌው ለአዲሱ ርዕሰ መስተዳድርም መልካም የስራ ዘመንን ተመኝተዋል። የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ የድርጅት ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ፈንታ ደጀን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ አቶ አያሌው ጎበዜ ባቀረቡት ጥያቄን እና የድርጅቱን የመተካካት መርህን መሰረት በማድረግ ወደ ሌላ ሀላፊነት ተዘዋውረዋል። አቶ ብናልፍ አንዱዓለምም የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር ሆነዋል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊ በመሆን ደግሞ ዶክተር አምባቸው መኮንን ተሹመዋል። የሙያና ቴክኒክ ኢንተርፕራይዞች፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የውሃ እንዲሁም የአከባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ቢሮዎች አዳዲስ ሀላፊዎችም በምክር ቤቱ ተሹመዋል።

No comments:

Post a Comment