Sunday, 22 February 2015
‹‹ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል›› በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን ‹‹የሚያልፉት በዕጣ ነው›› የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ‹‹ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡›› ተብሏል፡፡images
ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡›› ብለዋል
ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ”ሠማያዊ ፓርቲ ከ200 በላይ እጩዎች ተሰረዙብኝ አለ” በሚል ርዕስ አዲስ አድማስ እንደዘገበው —
”የፓርላማ ምርጫ እጩዎች ኢህአዴግ 501፣ መድረክ 303፣ ኢዴፓ 280
የሌላ ፓርቲ አባላትን በእጩነት አስመዝግቧል” – ምርጫ ቦርድ
ሠማያዊ ፓርቲ በተለያዩ ክልሎች ለፓርላማ ካስመዘገባቸው 400 እጩዎች ግማሽ ያህሉ በምርጫ ቦርድ እንደተሠረዙበት ሲገልፅ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ ሰማያዊ ፓርቲ ለምርጫው የሌላ ፓርቲ አባላትን ማስመዝገቡ ህገወጥ እንደሆነ ገለፀ፡፡
ለፓርላማ ኢህአዴግ 501 እጩዎችን፣ መድረክ 303 እጩዎችን፣ ኢዴፓ 280 እጩዎችን አቅርበዋል፡፡ ለፓርላማ ካስመዘገብናቸው እጩዎች ከሁለት መቶ በላይ ተሰርዘውብናል ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወላይታ፣ በቤንሻንጉል፣ በምዕራብ ጐጃም፣ በከምባታ፣ በሲዳሞ፣ በጋሞጐፋ፣ በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ጐንደር እና በሌሎች አካባቢዎች አሣማኝ ባልሆነ ምክንያት እጩዎቻችን ከምርጫ ውጪ ተደርገውብናል ብለዋል፡፡
ፓርቲው የምርጫ አስፈፃሚዎችን እንዳነጋገረ ኢ/ር ይልቃል ጠቁመው፤ እጩዎቻችንን የተሰረዙት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጣ ትዕዛዝ እንደሆነ ተነግሮናል ብለዋል፡፡ “የሌሎች ፓርቲዎችን አባላት አስመዝግባችኋል፤ ትብብር የሚባል ህገ ወጥ አደረጃጀት መስርታችኋል የሚሉ ምክንያቶችንም ሰምተናል ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ በአዲስ አበባ የተሠረዙብን እጩዎች ግን ግልፅ ምክንያት አልተሰጣቸውም ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከፓርላማ ምርጫ የተሠረዙት እጩዎች የተሠረዙበት ምክንያት እንዲነገራቸው ጠይቀዋል፤ ምርጫ አስፈፃሚዎች የሰጡን ምላሽ፤ “እናንተን ለመመዝገብ እኛ ችግር የለብንም፤ ግን እንዳንመዘግብ ከበላይ አካል ታዘናል፤ በደብዳቤ ምላሽ ልንሠጣችሁ አንችልም” የሚል ነው ብለዋል – ኢ/ር ይልቃል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከምርጫ ቦርድ ማብራሪያ ለማግኘት እንደሞከሩና፤ የቦርዱ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ነጋ ዱሪሳ በማመልከቻ ካልጠየቃችሁ መልስ አልሰጥም እንዳሏቸው ኢ/ር ይልቃል ተናግረዋል፡፡
የእጩዎች ስረዛን በተመለከተ ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ በሰጡት ምላሽ፤ “የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት” የተሰኘ ፓርቲ አባላቱን በሰማያዊ ፓርቲ ስም በእጩነት እንዳስመዘገበ በመግለፁ ነው ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን ማጣራት የጀመረው ብለዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ በማያውቀው ሁኔታ ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር መስርቻለሁ በሚል መንፈስ፤ የበርካታ ፓርቲዎች አባላት በሰማያዊ ፓርቲ ስም እጩ ሆነው ቀርበዋል ያሉት አቶ ወንድሙ፤ የደቡብ ኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ሊቀመንበር ራሳቸው በሰማያዊ ፓርቲ ስም አዲስ አበባ ላይ ተመዝግበው መገኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አንድ ፓርቲ የሌላን ፓርቲ አባል በእጩነት ማስመዝገብ አይችልም፤ ህገወጥ ነው ያሉት የምርጫ ቦርድ ም/ኃላፊው፤ ስለዚህ የአንድ ፓርቲ አባል በሌላ ፓርቲ ስም እጩ መሆን ስለሌለበት አጣርታችሁ መዝግቡ የሚል መመሪያ አስተላልፈናል ብለዋል፡፡
ቦርዱ የሰጠው መመሪያ እጩ እንዳትመዘግቡ የሚል ሳይሆን እያጣራችሁ መዝግቡ የሚል ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በዚህ አሰራር ደስተኛ ያልሆነ ማንኛውም ፓርቲ፤ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ቅሬታውን ከምርጫ ጣቢያ እስከ ምርጫ ቦርድ በየደረጃው ማመልከት እንዲሁም ለፍ/ቤት አቤቱታ አቅርቦ ውሳኔ ማግኘት ይችላል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢህአዴግ፤ ለፓርላማ 501፣ ለክልል ምክርቤቶች ከ1300 በላይ እጩዎችን አቅርቧል፡፡ አራት ፓርቲዎች የተጣመሩበት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ ለፓርላማ 303፣ ለክልል ም/ቤቶች ከ800 በላይ እጩዎችን ያቀረበ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) 168 እጩዎችን ለፓርላማ 475 እጩዎችን ለክልል ምክር ቤት አስመዝግቧል፡፡
በኢትዮጵያ ማህበረ ዲሞክራሲ – ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲም 83 ለፓርላማ 273 ለክልል ማቅረቡን ጠቁሟል፡፡ ሌላው የመድረክ አባል አረና ፓርቲ 33 እጩዎች ለፓርላማ 70 ለክልል አቅርቧል፡፡ ኢዴፓ በበኩሉ 280 እጩዎችን ለፓርላማ 200 እጩዎችን ለክልል አስመዝግቧል፡፡ ”
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment