Thursday, 25 December 2014
በነ ሀብታሙ አያሌው የክስ ጉዳይ የተሰየመው ችሎት ‹አስገራሚ› ውሎ
∙ተከሳሾቹ ‹‹ዘረፋ›› ተፈጽሞብናል ብለዋል
∙‹‹ለማን አቤት ይባላል?›› ሀብታሙ አያሌው
በላይ ማናዬ
ዛሬ ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር፡፡ የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች ተሟልተው ፍርድ ቤት ተገኝተዋል፡፡
ችሎቱ የተሰየመው ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ተከሳሾች በቀረበባቸው የሽብር ክስ ላይ የሰጡትን መልስ በተመለከተ 7ኛ ተከሳሽ መልስ በዕለቱ ባለማቅረባቸው አሟልተው እንዲቀርቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች በእስር ላይ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ እየተደረጉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ስለነበር ይህን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት ማብራሪያውን ለመስማት ነበር፡፡
የተከሳሾች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በጥየቃ ወቅት በተለየ መዝገብ ይመዘገባሉ የተባለውን አቤቱታ በተመለከተ፣ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በደብዳቤ መልስ መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ‹‹ማረሚያ ቤቱ በሰጠው መልስ እስረኞች ከሌሎች በተለየ የደረሰባቸው ችግር የለም›› ማለቱን ገልጾ ይህንኑ መልስ ሙሉ ለሙሉ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በዛሬው የችሎቱ ውሎ ላይ ተከሳሾች ለየት ያለ አቤቱታ በጠበቆቻቸው በኩል አቅርበዋል፡፡ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ለችሎቱ እንዳስረዱት ደንበኞቻቸው ከሌሎች በተለየ መልኩ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ አቶ ተማም አባቡልጉ በታህሳስ 12 ለ13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ሌሊት ስምንት ሰዓት ጀምሮ ደንበኞቻቸው ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የግል ማስታወሻዎቻቸው፣ ገንዘብ እና በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ እያዘጋጁት የነበረው መቃወሚያና መከራከሪያ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡
‹‹ደንበኞቼ ላይ እየተደረገ ያለው ጉዳይ ለህይወታቸውም የሚያሰጋቸው ነው፡፡ በማረሚያ ቤቱ በሌሊት ፍተሻ ያደረጉባቸው ሰዎች ቀደም ሲል በምርመራ ወቅት ‹ህገ-ወጥ› ተግባራት ሲፈጽሙባቸው የነበሩ የፌደራል ፖሊስና የደህንነት አባላት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ደንበኞቼ ያውቋቸዋል፡፡ ስለሆነም ፍተሻው የተከናወነው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አልነበረም ማለት ነው፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው የተለየ የስም ዝርዝር ተይዞ ከሌሎች በተለየ መልኩ ነው፡፡ ለአብነት ደንበኞቼ አቶ አብርሃ ደስታና በሌላ የክስ መዝገብ የተከሰሰው አብዱራዛቅ አክመድ ላይ የሆነው ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ነው፡፡ ፍተሻው ስለት ነገር አልያም ሌላ ህገ-ወጥ ቁሳቁስ ለመያዝ የተደረገ አለመሆኑን ከተወሰዱት ንብረቶች ማየት ይቻላል›› ሲሉ አቶ ተማም ለፍርድ ቤቱ በደንበኞቻቸው ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አስረድተዋል፡፡
ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ‹‹ማረሚያ ቤቱ መንግስት ዜጎች ታንጸው እንዲወጡ ያሰራው ነው፡፡ ይህን አሰራር ለመጠበቅም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የተለያዩ ስራዎችን ሊሰራ ይችላል፡፡ እየቀረበ ያለው አቤቱታም ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ነው›› ብለዋል፡፡
ጠበቃ ተማም የደንበኞቻቸውን አቤቱታ ከህግ አንጻር ያስረዱ ሲሆን፣ ‹‹በመሰረቱ ፍተሻ ሊካሄድ መቻሉ ላይ አይደለም አቤቱታው፡፡ የተካሄደው ፍተሻ ግን ህገ-ወጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍተሻው የተከናወነበት ሰዓት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ሳይሆን ሌሊት 8 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ይህ ህገ-ወጥ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ፍተሻው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አይደለም የተከናወነው፡፡ በደህንነቶችና የፌደራል ፖሊሶች ነው ፍተሻው የተደረገው፡፡ ይህም ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ብቃቱ እንደሌለው ያሳያል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ይህን መሰል ድርጊት የፈጸሙት አካላትና በማን ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡
ጠበቃ ተማም በተጨማሪ ከደንበኞቻቸው ላይ በፍተሻው ወቅት የተወሰዱባቸው ንብረቶችና ማስታወሻዎች እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ‹‹የተለየ ከፍተኛ በደል ደርሶብኛል›› በሚል ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበሩት 3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የጠየቁት የመናገር እድል ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል፡፡
በጠበቆቹ አማካኝነት የቀረበው አቤቱታን በተመለከተ ችሎቱ አስተያየት የሰጠ ሲሆን በተለይ ጠበቃ ተማም አቤቱታውን ባቀረቡበት ወቅት ‹‹ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎትም ብቃትም የለውም›› ያሉት አገላለጽ ተገቢ ስላልሆነ እንዲታረሙ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በቃል የገለጹት የመሐል ዳኛው፣ ‹‹እንዲህ አይነት አገላለጽ ማረሚያ ቤቱ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፋ እንዳይሆን…›› በማለት ሌላ አስገራሚ መነጋገሪያ ከፍተዋል፡፡
ይህን የዳኛውን ንግግር ተከትሎ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌው የመናገር እድል ከተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ ለአጭር ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡ እናም፣ ‹‹እርስዎ እያሉት ያለው ነገር ተገቢ አይደለም፡፡ በህይወቴ ላይ የደህንነት ስጋት አለብኝ ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ይህንን ስጋቴን ለችሎት እያስረዳሁ ነው፡፡ ግን እርስዎ ‹የበቀል እርምጃ› እንዲወሰድብን ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ በእርግጥ አሁንም የበቀል እርምጃ እንደማይወሰድብን ማረጋገጫ የለንም፡፡ እሺ ለማን አቤት ይባላል? የደረሰብንን በደል ለፍርድ ቤት ከማስረዳት ውጭ ለማን አቤት እንላለን….አሁን እኮ ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤቱ ጋር መወገኑን ነው እያየን ያለነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የእኛን አቤቱታ እየሰማ አይደለም፡፡ ከፍርድ ቤት ውጭ ለማን አቤት እንበል?›› ሲል አቤቱታውን በስሜት ውስጥ ሆኖ አስረድቷል፡፡
የሀብታሙን ንግግር አዳምጠው አንደኛ ዳኛ ‹‹እኛ ሳንሆን ህጉ ነው ይህን እንድንል የሚያደርገን›› በማለት አጭር መልስ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መልኩ ቀጥሎ የዋለው ችሎት በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ፍርድ ቤቱ ይህን ጉዳይ የማየት ስልጣን አለው ወይስ የለውም በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት፣ እና መደበኛ ክሱን ለማየት ለታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተጥቷል፡፡
Saturday, 6 December 2014
Monday, 1 December 2014
ከ40 በላይ የአንድነት አባላትና አመራሮች በቃሊቲ እስር ቤት ታገቱ
የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃን ጨምሮ ከአርባ በላይ የሚሆኑ የፓርቲው አባላት ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ታገቱ፡፡
አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪ ቃል ከህዳር 14 ጀምሮ እያካሄደያለው የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የህሊና እስረኞችን የመጎብኘት መርሀ-ግብር ለመሳተፍ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ያቀኑት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃ እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶነገሰ ተፋረደኝን ጨምሮ 40 የአንድነት ፓርቲ አባላት ለግዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሰበብ በእስር ቤቱ ግዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ከስፍራው ዘግበዋል፡፡
አንድነት የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪቃል በዚህ ሳምንት እያካሄደ ያለው ንቅናቄ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ትኩረት ማግኘቱ ገዢውን ቡድን ማስቆጣቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ዘግይቶ የደረሰን ዜና እንዳመለክተው ከሆነ ደግሞ; የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፈረደኝ፣ ንዋይ ገበየሁ፣ ዳንኤል ሙላትና አቶ ብርሐኑና ትግስት ክራውን ሆቴል አካባቢ አሁንም ታስረው እንደሚገኙ ምንጮች ገለጹ፡፡
ስማቸው ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች የታሰሩ የህሊና እስረኞችን ለመጠየቅ ወደቃሊቲ አምርተው ከነበሩት ሰዎች መካከል ይገኛሉ፡፡
Wednesday, 26 November 2014
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አመራሩ ድብደባ እንደተፈጸመበት ገለፁ።
አንድ ወር የትግል መርሃ ግብር ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችና ህዝባዊ የለውጥ ንቅናቄዎችን በገዥው ፓርቲ አፈና እና ማስፈራሪያ እንደማይቆም ትብብሩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ህዳር 7/2007 ዓ.ም የትብብሩ ህዝባዊ የአደባባይ ስብሰባ በኃይል መበተኑን፣ ይህንኑ አስመልክቶ ህዳር 7/2007 ዓ.ም ለሰማያዊ ፓርቲ ማስጠንቀቂያ መጻፉን እና ለህዳር 21 ለሚደረገው ስብሰባ የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ደብዳቤ በፖስታና በአካል ቢላክለትም ማሳወቂያ ክፍሉ አልቀበልም ማለቱን የገለጸው መግለጫው ስርዓቱ የትብብሩን የትግል መርሃ ግብር ለማስቆም እየጣረ መሆኑን ገልጾአል፡፡
በተጨማሪም የትብብሩ አንድ አባል እና ትብብሩ ህዳር 21/2007 ዓ.ም የሚያደርገውን የአደባባይ ስብሰባ የሚያስተባብረው መኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ የሆኑትን አቶ ኑሪ ሙደሲር ላይ የድብደባ ወንጀል እንደተፈጸመባቸው አመራሩ ገልጸዋል፡፡
ትብብሩ በዛሬው ዕለት ‹‹ማስፈራራትና አፈና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችንና ሠላማዊ ሕዝባዊ የለውጥ ንቅናቄዎችን አይቀለብስም›› በሚል በሰጠው መግለጫ የተገኙት አቶ ኑሪ ሙደሲር ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ወከባ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ኑሪ ‹‹መኪናችን ገጨህብን ባሉ 10 ሰዎች ነው የተደበደብኩት፡፡ ከአሁን ቀደምም ፖሊሶች ምንም አይነት ችግር ሳላደርስ ገጨህብን ብለው አዋክበውኛል፡፡ ሰሞኑን መኪናዬን ቢሰብሩብኝም በስህተት የተመታ መስሎኝ ነበር፡፡ አሁን ከደበደቡኝ መካከል ተክለኃይማኖት አካባቢ የሚገኙ ካድሬዎችና ደንብ አስከባሪዎች ይገኙበታል፡፡ መጀመሪያ ላይ ፖሊሶች ‹ቢገጭስ እንዴት 10 ሆናችሁ አንድ ሰው ትደበደርባላችሁ?› ካሉ በኋላ እንደገና ካድሬዎች መሆናቸውን ሲያውቁ እነሱን ትተው እኔን ይወቅሳሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር መሆኑን ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ህዳር 21/2007 ለሚደረገው የአደባባይ ስብሰባ በአካልም ሆነ በፖስታ ደብዳቤ ቢላክም የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ባለመቀበሉ የትብብሩ ደብዳቤ በፋክስ እንዲደርሰው እንደተደረገ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በፋክስ የተላከውን ደብዳቤ አልቀበል ካለ የትብብሩ አመራሮች በጋራ ደብዳቤውን ለማድረስ እንደሚሄዱ፣ የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ይህንም አልቀበልም ካለ ሁነቱን በቪዲዮና በፎቶ በመቅረጽ ለህዝብ በማሳወቅ ስብሰባውን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በሂደቱም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል እንደተዘጋጁ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
Saturday, 22 November 2014
Friday, 14 November 2014
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፖሊስ ጣቢያዎችን እንዲሰሩ ተጠየቁ
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በየ አካባቢያቸው ለሚሰሩት አዳዲስ ፖሊስ ጣቢያዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ መጠየቃቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ በየ አካባቢው የሚገኙት የፖሊስ ጣቢያዎች ነዋሪዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ በየ ቤታቸው ደብዳቤና የገንዘብ መክፈያ ቅጽ እየሰጡ ሲሆን ነዋሪዎቹ ገንዘብ እንዲከፍሉ የተጠየቁበትን ቅጽ ሳይሞሉ መመለስ አይችሉም ተብሏል፡፡
ደብዳቤው ላይ ባለው የፖሊስ ጣቢያው ስልክ ቁጥር ደውለን ያነጋገርናቸውና ስማቸውን ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆኑ አንድ የፖሊስ አባል ‹‹ህዝቡን ለምን ፖሊስ ጣቢያ እንዲሰራ ታስገድዳላችሁ?›› በሚል ላነሳነላቸው ጥያቄ ‹‹ህዝቡኮ ራሱ ነው ሴት ልጆቻችን በሰላም መግባት አልቻሉም እያለ ያለው፡፡ ፖሊስ የህዝብ እስከሆነ ድረስ ህዝብ ፖሊስ ጣቢያ ቢያሰራ ምን ችግር አለው? ህዝቡ አልከፍልም ካለ ሊቀር ይችላል፡፡ እናንተ ግን ይህን እንደጥያቄ የምታነሱት ስብሰባው ላይ ስላልነበራችሁ ነው፡፡›› ብለውናል፡፡
ከወራት በፊት ‹‹ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ›› በሚል አደረጃጀት ህዝቡ በየቤቱና ከጎረቤት ጋር 1ለ5 በመደራጀት ከፖሊስ ጋር ግንኙነት እንዲኖረው የሚያዝ ህግ መውጣቱና ነዋሪዎቹንም ማደራጀት መጀመሩን ነገረ ኢትዮጵያ መዘገቧ ይታወቃል፡፡
Wednesday, 12 November 2014
የፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ልዩ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ ተነሱ፡፡
የፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ልዩ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ ተነሱ፡፡ አቶ አሰፋ የተነሱት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡ በአቶ ኃይለ ማርያም ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ አቶ አሰፋ ከኃላፊነት የተነሱበትን ምክንያት ያልጠቀሰ ሲሆን፣ አቶ አሰፋም በምን ምክንያት እንደተነሱ እንዳላወቁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ወደፊት የሚተገበሩ አዳዲስ ፕሮግራሞችን እየቀረፅኩ ነበር፤›› በማለት ከኃላፊነት መነሳታቸው ያላሰቡትና ያልጠበቁት እንደሆነ አቶ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ደብዳቤው በጥቅሉ፣ አቶ አሰፋ ከኅዳር 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናውን ገልጿል፡፡
በሥራ አፈጻጸምም ሆነ በሙስና እንዳልተገመገሙ አቶ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸው፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አዲስ የሥራ መደብ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ መጻፉን ተናግረዋል፡፡
የሸካ ዞን፣ የኪ ወረዳ፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ የነበሩት አቶ አሰፋ፣ የክልሉ ፀረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነርና የደቡብ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለአምስት ዓመታት የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡ አቶ አሰፋ የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ ከመሆናቸው በፊት፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሆነውም ሠርተዋል፡፡
አቶ አሰፋ የፍትሕ ሚኒስቴርን ለሦስት ዓመታት ከመሩ በኋላ ከቦታው ተነስተው የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ ሆነው ተሰይመዋል፡፡
አቶ አሰፋ ላለፉት ስድስት ዓመታት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስንና በቅርቡ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ሲያማክሩ ቆይተዋል፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)




