Thursday, 13 February 2014

የጋዜጠኛው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩን አስቆጣ

ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጽ/ቤታቸው ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ታምራት ገብረጊዮርጊስ በቀረበላቸው ጥያቄ በመቆጣት ዘለፋ ሰነዘሩ፡፡ አቶ ታምራት ለጠ/ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ በአሁን ሰዓት አገሪትዋን የሚመራት ማንነው ነው የሚል ይዘት ያለው ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩም ብስጭታቸውን በምላሻቸው ወቅት አንጸባርቀዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጋዜጠኛውን ሂድና እዚያ ሐሜት የምትጽፍበት ገጽ ላይ ጻፈው በማለት መዝለፋቸው በርካታ ጋዜጠኞችን አስደንግጦአል፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞች ስለሁኔታው በሰጡት አስተያየት ጋዜጠኛ ታምራትን በማድነቅ አንድ ጋዜጠኛ በሕዝብ ውስጥ የሚነገርን ጥያቄ አውጥቶ መጠየቁ ተገቢና ሙያዊ ሃላፊነቱ መሆኑን በመጥቀስ ጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄው የቱንም ያህል ቢያበሳጫቸው በዚህ መልኩ ምላሽ መስጠታቸው ራሳቸውን ከማስገመት ያለፈ ትርፍ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ከአቶ መለስ ሞት በሃላ ወደስልጣን የመጡት አቶ ኃይለማርያም ቀደም ሲል በአቶ መለስ ብቻ ሲመራ የነበረውን የጠ/ሚኒስትር ስልጣን የጋራ አመራር በሚል ፈሊጥ ሶስት ቦታዎች በመክፈልና በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ ለኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስልጣናቸው ማከፋፈላቸው በሕዝብ ዘንድ ያለስልጣን የተቀመጡ አሻንጉሊት መሪ እስከመባል አድርሶአቸዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው ብዙ ሲባልበት የቆየውን ኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ ከውይይት ያለፈ ነገር እንደሌለ በመናገር የሚደርስባቸውን ትችቶች ያጣጣሉ ሲሆን አጀንዳውንም ከመጪው ምርጫ ጋር በማያያዝ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ መሆኑን ለመናገር ሞክረዋል፡፡ በኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ በስፋት የዘገቡትና ሒደቱንም ያሳወቁት የሱዳን ጋዜጦች መሆናቸውን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡ ከኢህአዴግ ጋር በመደራደር አገር ውስጥ ገብተዋል ስለተባሉትም አቶ ሌንጮ ለታ ተጠይቀው ዋሽንግተን ለሚገኘው ኢትዮጽያ ኤምባሲ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ከመስማታቸው ውጪ ስለመግባታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመናገር ጉዳዩን አስተባብለዋል፡፡

Tuesday, 11 February 2014

የአዲስ አበባ ከንቲባና ፖሊስ ኮሚሽነር በ“አንድነት” ተከሰሱ

ከንቲባ ድሪባ ኩማና ኮሚሽነሩ መከራከሪያቸውን ለፍ/ቤት ያቀርባሉ አንድነት፣ የመንግስት አካላትን በተከታታይ እከሳለሁ ብሏል አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት)፣ የአዲስ አበባ ከንቲባና የፖሊስ ኮሚሽነራቸው ላይ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሰረተ ሲሆን ተከሳሾች መልሳቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ለየካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጠ፡፡ አንድነት ፓርቲ፤ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የተሰኘ አገር አቀፍ የ3 ወር ንቅናቄ ማጠቃለያን በአዲስ አበባ ባካሄደበት ወቅት በከተማ አስተዳደሩና በፖሊስ ኮሚሽን እስርና ወከባ እንደተፈፀመበት ገልፆ፤ በደላቸውን በማስረጃ በመዘርዘር ክስ መመስረቱን አስታውቋል፡፡ በፖሊስ ተፈፀመ በተባለ በደል ከንቲባውን በቀጥታ ለምን እንደከሰሰ ፓርቲው ሲያስረዳ፣ የአዲስ አበባ መተዳደሪያ ቻርተር ከንቲባው የከተማዋን ፖሊስ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ስለሚደነግግ ከንቲባውን በቀጥታ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ብሏል፡፡ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት በጅምላ በፖሊስ ታስረው መዋላቸውን ፓርቲው ጠቅሶ፣ የቅስቀሳ ቁሳቁስ ተነጥቀናል፤ ፖስተሮችን እንዳንለጥፍ ተከልክለናል ብለዋል። የፖሊስን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የመከታተል ሃላፊነት የተጣለባቸው ከንቲባውና ኮሚሽነሩ፣ የፖሊስን ህገወጥ ተግባር በቸልታ አልፈውታል ብሏል – አንድነት ፓርቲ፡፡ “በቂ ማስረጃ ከተደራጀ በኋላ ነው ወደ ክስ የሄድነው” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ ክሱን የመሰረቱት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ እና ረዳታቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከንቲባውና ኮሚሽነሩ የካቲት 24 ቀን መልሳቸውን ካቀረቡ በኋላ መጋቢት 2 ቀን ክርክር ይካሄዳል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍ/ቤት የለም ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት የፓርቲው መሪዎች፤ የመንግሥት አካላት የሚፈፅሙትን አፈና በይፋ ወደ ፍ/ቤት በመውሰድ የፍትህ ስርአቱን መፈተንና ለህዝብ ማጋለጥ አንዱ የትግል አላማችን ነው ብለዋል፡፡ ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2005 ለ3 ወራት፣ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል በመላ አገሪቱ የተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ህዝብን በማነቃቃት ስኬታማ ውጤት አግኝተንባቸዋል ሲሉ የፓርቲው መሪዎች ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በፀጥታው ኃይል እና በገዢው ፓርቲ ካድሬ መካከል ልዩነት አለመኖሩን አይተናል፤ በአገሪቱ በተዘረጋ የአፈና መዋቅር ከፍተኛ የህግ ጥሰት እንደሚፈፀም አረጋግጠናል ያሉት የፓርቲው መሪዎች፤ የመንግስት ጫና ሳያሸብረው ፓርቲው ተመሳሳይ ንቅናቄዎችን በተከታታይ ያዘጋጃል ብለዋል፡፡ “የፀረ-ሽብር አዋጁን ለማሰረዝ የሰበሰባችሁትን ድምፅ የት አደረሳችሁት” የሚል ጥያቄ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸው አመራሮቹ፤ “የተሰበሰበውን የህዝብ ድምፅ ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ የህግ ባለሙያዎች እየመከሩበት ነው፣ በሁለተኛ ዙር የክስ ሂደት ውስጥ የሚካተት ይሆናል ብለዋል፡፡ በተካሄደው የ3 ወር የህዝብ ንቅናቄም መንግሥት ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ፓርቲው ጫና ማሳረፉን የሚያመለክቱ ውጤቶች መታየት መጀመራቸውን የጠቀሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው፤ የፀረ-ሽብር አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ለህዝብ ውይይት መቅረብ ሲገባው አዋጁ ወጥቶ ብዙዎችን ሰለባ ካደረገ በኋላ መንግስት ራሱን ለመከላከል የፕሮፖጋንዳና የስልጠና ዘመቻ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ይህም ፓርቲያቸው ይዞት የተነሳው ጥያቄ ጫና ማሳረፉንና ትክክለኛ እንደነበር የሚያረጋግጥ መሆኑን አቶ ሃብታሙ ገልፀዋል፡፡ “ማንም ሰው ወይም አካል ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም” ያለው ፓርቲው፤ ህግ በሚጥሱ የመንግስት አካላት ላይ በተከታታይ ክስ እመሰርታለሁ፤ በቅርቡም በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና በገዢው ፓርቲ ላይ ተጨማሪ ክስ ለመመስረት እየተዘጋጀሁ ነው ብሏል፡፡

Wednesday, 5 February 2014

ወያኔ: የነፃው ፕሬስ ፀር!

ነፃ- ፕሬስ ለነፃነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት የሚኖረውን አስተዋፅኦ የሚገነዘቡ ገዢዎች ፕሬሱ ለአንባገነንነት አገዛዛቸው የሚመች ስለማይሆን ይፈሩታል፤ ይጠሉታል፤ ያጠፉታል። ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው። ነፃ ፕሬስ የሀሳብ ነፃነት መብት አልፋና ኦሜጋው ነው ብል ማጋነን አይሆንም። የነፃ ፕሬስ መኖር የሚያረጋግጠው ጋዜጠኞች ያለምንም ጭንቀትና ፍርሃት የሚያስቡትን፡ የሚሰማቸውን፡ የሚሰሙትን እንዲሁም ምርምር አድርገው የደረሱበትን ዜናዎች በነፃ ለመፃፍና ለማሰራጨት ብሎም ሕዝብ እንዲወያይበት ለማድረግ ያላቸው ያልተገደበ መብት ነው። ይህም ጤናማ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ለእድገቶቹም ጉልህ ድርሻ አለው። ነፃ ፕሬስ የኃሳብ ነፃነት ተግባራዊ ለመሆኑ ዋስትናም መፈተኛም ነው። ኃሳብን ያለምንም ጭንቀትና ፍርሃት በነፃ ለመግለፅ መቻልና መለዋወጥ እንደ ምግብና መጠጥ፤ ሁሉ ሰብአዊ ክቡርነትን የተላበሰ ሕይወት ለመጎናፀፍም አስፈላጊም ናቸው። ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት መኖርና ዋስታናው ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሕግ መረጋገጥ ማለት ዘላቂነት ላለው ዴሞክራሲያዊ እድገት ለማገኘትም ዋና መሰረት ነው። የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የነፃ ፕሬስ አስፈላጊነት ትልቅ ቦታ እንዳለው ከልብ ይታመናል፡፡ ያለነፃ ፕሬስ ዴሞክራሲ አለ ብሎ መናገር ማወናበድ እንጅ እውነት ሊሆንም አይችልም፡፡ የነፃ ፕሬስ መኖር በራሱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መኖር መገለጫ ነውና፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲኖርም ነፃ ፕሬስ ይኖራል፡፡ ወደ እኛ ሃገር ስመለስ ግን ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ወያኔ መንግስት ሆኖ ላለፉት 23 ዓመታት ሃገሪቱን ሲያስተዳድር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በወረቀትና በቃል እንጂ ከዚያ በዘለለ በተግባር ሲፈፅም አላሳየንም፡፡ ለመተግበር የሞከራቸውንም እንደ ቀንዳውጣ ቀንድ መልሶ ሸሽጎታል፡፡ ስለዚህ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማያምን አምባገነን ስርአት ስለሆነ ለነፃው ፕሬስ ፀር በመሆን ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በመስጠት ፋንታ አጥፊና ደምጣጭ ሆኖ እየሰራ ይገኛል። ዛሬ በዘመነ ወያኔ በኢትዮጵያችን ነፃ ፕሬስ በአሳሪና አስፈሪ የፕሬስ አዋጅ ተጠፍሯል። ጋዜጠኞች ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በየፍርድ ቤቱ እየተጎተቱ ነው። ወደ እስርቤት እየተጣሉ፤ እየተሰደዱም ነው። የጋዜጣ፣ የመጽሔት፣ የመጻሕፍት ማሳተሚያ ዋጋ ሰማይ ጠቅሷል። በሀገሪቱ ሕገመንግሥት ቀርቷል የተባለ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ጓሮ በኩል በእጅ ኣዙር ተመልሶ እንዲመጣ ተደርጔል። ሌሎች በከተማው ያሉ ማተሚያ ቤቶችም ሳንጃ የተከለ ጠመንጃ ወድሮ የሚያስፈራራ ኃይል ያለባቸው ይመስል “የተቃዋሚ ጋዜጣን አናትምም” ብለዋል። በቅርቡ በሰማያዊ ፖርቲ ‘‘ነገረ ኢትዮጵያ’’ ጋዜጣ ላይ የተሰተዋለው ችግር ይሄው ነው። ጋዜጣዋ ተዘጋጅታ ለማተምያ ቤት ብትበቃም ስርአቱ በፈጠረው የማደናቀፍ ተንኮል ለህትመት ሳትበቃ በመቅረቷ በፓርቲው ቀና ትብብር በድህረ ገፃቸው እንድናገኛት ተገደናል። ማተሚያ ቤቶች ሠርቶ የማትረፍና ሀብት የመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲሁም ሕዝብን የማገልገል ግዴታቸውን በፍርሀት ጨርቅ ገንዘው በየማተሚያ ቤታቸው ጓሮ ቀብረውታል። የሕዝብ ንብረት የሆኑ፣ በሕዝብ ሀብት የሚተዳደሩ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሃያ አራት ሰዓት በወያኔ በሞኖፖል ተይዘዋል፡ የገዥው ልሳን ብቻ መሆናቸውንም አስመስክረዋል። ሌሎችም የተለያየ ስም እየተሰጣቸው በአየር ላይ አለን የሚሉ ጣቢያዎች ልሳናቸው የበዛ ቢመስልም ከሞላ ጎደል ቋንቋቸው አንድ ነው። ያ ቋንቋ ግን የእውነተኛ ነፃ ፕሬስ ቋንቋ አይደለም። በዚህ ዓይነት የፕሬስ ሁኔታ በሀገራችን ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም። negere ethiopiaይህ ነፃ ፕሬስን ማቀጨጭ ብሎም ለመቃብር ማብቃት ደግም በአለም ላይ በስፋት እንደታየው የአምባገነን መንግስታት መለዬ ካባ ነው። አምባገነኖች የሚገዙትን ህዝብ ለመቆጣጠር ከሚወስዷቸው እርምጃዎች ቀዳሚው ፕሬስን መቆጣጠር ነው። በጉልበት የሚገዙት ህዝብ እነሱ ከሚሉት ውጭ እንዳይሰማ ለማድረግ ወደ ህዝብ ጆሮ የሚደርሱትን ነገሮች ሁሉ የመቆጣጠር ተግባር ይፈጽማሉ። ከዚህም በተጨማሪ ውሸትን ደጋግሞ በማውራት እውነት ለማስመሰል ይተጋሉ። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች ሁሉ የጋራ ባህርይ ነው። ስለዚህ ወያኔም ነፃ ፕሬስን የሚፈራበት ትልቁ ምክንያት በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት አምባገነንነቱንና የጥፋት ተልዕኮ ሚናውን አጋልጠው በሕዝብ እንዲተፋ ማድረጋቸውን በሚገባ ስለሚያውቅ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ነፃ ፕሬሶች ወያኔን ከሥልጣን ለማስወገድ በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን በማወቁ ጭምር ነው። ወያኔ ለሙያቸው ክብር ያላቸው ጋዜጠኞችን በክሶች ብዛት፤ በእስርና እንግልት እንዲሁም ከአቅማቸው በላይ በሆነ የገንዘብ ቅጣት እንዲሸማቀቁ በማድረግ እውነት ዘጋቢ ስታጣ የኢትዮጵያ የመረጃ አየር በውሸት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል። ወያኔ በፈለገው መልክ ሊተረጉመው በሚችለው አንቀጽ ጋዜጠኞችን እያስፈራራና እያዋከበ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ነፃነት መብትን ይኸው እስካሁን ድረስ እንዳፈነ ይገኛል። ወያኔ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ለታሰሩ፥ ለተገደሉ፥ ለስደት ለተዳረጉ በርካታ ጋዜጠኞች ዋና ተጠያቂ ነው። የእስራት ፍርድ ተፈርዶባቸው በመማቀቅ ላይ የሚገኙ አሁንም በርካታ ናቸው። የተወሰኑትም ደግሞ ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርገዋል። በአገር ውስጥ የሚገኙ የመረጃ መረቦችን በማናለብኝነት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፤ ከውጭ አገራት የሚተላለፉ የሬድዮና የቴሌቪዥን ሞገዶችን በይፋ በማፈን ኢትዮጵያ አገራችን በመረጃ ከዓለም የተነጠለች ደሴት ለማድረግ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ሃብትንም ለዚህ እኩይ ስራው ያባክናል። ነፃ-ፕሬስ ለነፃነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት የሚኖረውን አስተዋፅኦ የሚገነዘቡ ገዢዎች ፕሬሱ ለአንባገነንነት አገዛዛቸው የሚመች ስለማይሆን ይፈሩታል፤ ይጠሉታል፤ ያጠፉታል። ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው። በመጨረሻም ወያኔ የነፃ ፕሬስ ጠላትነቱን ያረጋገጠው ሥልጣን እንደጨበጠ በመሆኑ ላለፉት 23 አመታት አንድን አፋኝ ሕግ በሌላ አፋኝ ህግ እየተካና እያጠናከረ የነፃ ፕሬስ ፀር መሆኑን ያስመሰከረ በኢትዮጵያ ላይ የመጣ መቅሰፍት ነው። ስለዚህ ለእውነት የቆመ ነፃ ሚዲያ መወለድና ማበብ በአገራችን እንዲኖር ለምንሻው ዲሞክራሲ የመሰረት ድንጋይ መሆኑን በማመን፤ ለእውነት የቆሙ ነፃ ፕሬሶች እንዲፈጠሩ መታገል የሁላችንንም ርብርብ የሚጠይቅ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ራሷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ያለ ነፃ ፕሬስ ማሰብ አይቻልምና:: መረጃ የተጠማው የኢትዮጵያ ህዝብም ነፃ የሚዲያ ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ እንቅፋት የሆነውን የአንባገነኑን የወያኔ አገዛዝ ከጫንቃው ለማውረድ በጋራ መታገል ይኖርበታል። በተጨማሪም ነፃ ፕሬስ ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በመረዳትና፤ መብትም በትግል እንደሚገኝ በማመን የፕሬስን ነፃነትን ለማምጣት በአንድነት በመነሳት እንቅፋት የሆነውን አገዛዝ በቃህ ልንለው ይገባል። በመረጃ የዳበረ ህዝብ አንባገነኖችን ቀባሪ ነው!

Tuesday, 4 February 2014

ESAT MY

https://www.facebook.com/photo.php?fbid=249629698541293&set=pcb.249630991874497&type=1&theater

Saturday, 1 February 2014

በጎንደር ክ/ሃገር ሳንጃ ወረዳ የልዩ ሃይል አዛዥ ሻለቃ ቀለሙ ክብረት መገደላቸው ተሰማ

(ዘ-ሐበሻ) በጎንደር ክ/ሃገር ሳንጃ ወረዳና አካባቢው ሕዝብን ሲያሰቃይ ነበሩ የተባለት የልዩ ሃይል አዛዥ ሻለቃ ቀለሙ ክብረት መገደሉ ተሰማ። የአርበኞች ግንባር ለግድያው ሃላፊነቱን ወስዶ “ግለሰቡ የተገደለው በጥር 21-2006 ዓ.ም ከቀኑ 12 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰርጎ ገቦች ማሰሮ ደንብ የተባለ ቦታ በጥይት ተደብድቦ ቆስሎ ወዲያውኑ ወደ ጎንደር ቸቸላ ሆስፒታል ቢወሰድም በማግስቱ ማለትም በጥር 22-2006 ዓ,ም ህይወቱ አልፏል።” ብሏል።
(የአርበኞች ግንባር ወታደር – ፎቶ ፋይል) እንደ አርበኞች ግንባር ገለጻ ከሆነ “ይህ ግለሰብ በወረዳው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአርበኞች ደጋፊ ናችሁ በሚል ሲያሰቃይ የነበረ ሲሆን፣ ብዙ ንፁሃን ግለሰቦችን በድርጅቱ ደጋፊነት ስም እየፈረጀ እንደገደለ፣ እንዳሰረና እንዲሰደዱ ሲያደርግ የነበረ መሆኑ ይታወቃል ። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ግለሰቡ ከድርጊቱ ታቅቦ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር ካልሆነ ግን አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድበት የፅሁፍ መልዕክት የደረሰው ቢሆንም ሊታረም ባለመቻሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰርጎ ገቦች እርምጃ እንዲወስዱበት ተደርጓል።” ብሏል።
(የአርበኞች ግንባር ሠራዊት በምረቃ ላይ – ፎቶ ከፋይል) “በጎንደር አካባቢ ምንም አይነት ወታደራዊ እርምጃ በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ሲወሰድ የአካባቢውን ሕዝብ ማንገላታቱ የተለመደ ቢሆንም ሻለቃ ቀለሙ ክብረት ከሞተበት ከትናንት ጀምሮ ግን በህዝቡ ከፍተኛ ስቃይ እያደረሰበትና ገዳዮቹን ታውቃላችሁ እናንተ ናችሁ እየደበቃችሁና ቀለብ እየሰፈራችሁ የምታስጨርሱን በሚል ብዙ ሰዎች እንደታሰሩ ታውቋል።” የሚለው የአርበኞች ግንባር ዜና “የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ወታደራዊ መምሪያ በበኩሉ ወደፊትም ቢሆን ወያኔና ተላላኪዎቹን ከዚህም በከፋ ሁኔታ አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣ አስታውቆ ሕዝቡም ከመሬቱና ከንብረቱ እየተፈናቀለ መኖሩ ያበቃ ዘንድ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ይህን አፋኝ ስርዓት ለመገርሰስ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለበት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” ብሏል። በዚህ ዜና ዙሪያ የመንግስትን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። http://www.zehabesha.com/amharic/archives/12396