Monday, 13 January 2014
ማገዶ!
እውነት ለመናገር ከዬካቲት በፊት በአጭር ጊዜ ላልመለስ ወስኜ ነበር። ብቻ እንዲህ ሆነላችሁ … ተክዤ ቆዬሁ። አፍጥጬም አዬሁት። ባለፉት ሳምንታት ዘሀበሻ ላይ የአንድነት ልዩ ጉባኤ ውጤትን ጀመርኩት። መጀመር ነበረብኝና ውስጤን አናጋርኩት – የግድ። የአዲሱን የአንድነት ልዩ ጉባኤ ተመራጮችን ዝርዝር አዬሁት። አቶ ሸፍጠኛው ሂደት …. አንተ ምን አለብህ ቀልድ። ዬደላህ! መለስህ መላስህ ግራጫ ያሰኛኃል …. ዛሬም አዲስ ትወና ይዘህ ከች … አታካች።
እርግጥ በሂደቱ የቀድሞ የአንድነት ምክትል ሊቀመንበር እሩቅ አሳቢው እስረኛው አቶ አንዱአለም አራጌ በጣም እንደ ተደሰተ ዘሀበሻ ላይም አንብቢያለሁ። በሌላ በኩልም ትናንትና በ07.01.2014 ዝርዝር መረጃ ስለመርጫው ሂደት „ከቃሌ ሩም“ አዳምጫለሁ። የቃሌ ሩም ከአቶ ሃብታሙ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደ አዳመጥኩት ከሆነ ምርጫው ዲሞክራሲ እንደ ነበረ ብቻ ሳይሆን አዲሱ አመራር በቃሊቲ እስር ቤት ከአቶ አንዱአለም አራጌ ጋር የነበረውን ቆይታ ምን ይመስል እንደነበርም በዝርዝር ተገንዝቤያለሁ። ያንገበገበኝ ጥቄ ይነሳል በማለት ጓጉቼም ነበር። የሆነ ሆኖ „አቶ አንዱአለም አራጌ ዘግይቶ ሊታይ የሚገባው የአማራሩ ጥንካሬ ከ15 ዓመት በፊት መቅደሙ እንደ አስደሰተው ከደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ጋር በንጽጽር ሲያው በጣምም እንደተደነቀ ተስፋም እንደጣለበት“ ነበር አቶ ሃብታሙ የገለጹት። መልካም ነው …
ይህ የበለጠ የገለጸልኝ ነገር ቢኖር የአቶ አንዱአለምን ቅንነትና አውንታዊ ዕይታ አመላክቶኛል። በሌላ በኩል ግን ይህ አዲስ መዋቅር ብቻውን የጥንካሬ መግለጫ ሊሆን ከቻላ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ እስር ቤት እያለች መሰሉ ተከነውኖ ስለነበር እኔ እመደነቀብት ምንም ጉዳይ የለም። …. ለአድናቆት ወይንም ተስፋን በሙሉ ጥግ ለመስጠት ነገን መጠበቄ ግን ግድ ይላል።
በነገራችን ላይ በትናንቱ ቃለ ምልለስ የተደስትኩበት አቶ ኃብታሙ ከወያኔ ጋር በነበረቸው አጭር የቤተኝነት የቆይታ ጊዜ „ በድዬ ከሆነ ይቅርታ የመጠዬቅ ሞራል አለኝ“ ማለታቸው አስተማሪ ነበር። ወጣትነት ሁሉንም ሞክሮ ማዬት በመሆኑ፤ ወጣቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የወያኔን መሰሪ ሀገርና ህዝብን የመግደል ሴራ መርምረው ይህን መሰል እርምጃ መውስዳቸው አብነት ነው ለእኔ። በቀጣይ የትግል ሂደትም በሚያሳዩት የነቃ ጉልህ ተሳትፎ ውስጣቸውን አንጥሮ ማሳዬት የሚችሉ ከሆነ መልካም ነው። እንዲህ ከወያኔ እጅ እያመለጡ የሚመጡትን ወጣቶች በአግባቡ ይዞ ሞራላቸውንም ጠብቆ የነፃነት ትግሉ ጽኑ ቤተኛ ማደረግ የሁላችንም ግዴታ ነው። ወጣትነት ብዙ ባህሪያት በህብር የሚገኝበት በመሆኑ በጥንቃቄ የአያዛዝ ጥበብን ይጠይቃል።
ሰሞኑን ስተኛ መገላበጥ አበዛሁ። ለምን? … ቀኑን አላስታውስም ብቻ „ጠርዝ ላይ ያለ ስጋቴ“ የሚል አንድ ጹሑፍ በአደራ ተርጓሚው፤ በቀጥተኛው፤ በግልጹና በግንባር ሥጋው …. በወጠት አንዱአለም አራጌ ዙሪያ የሆነ ነገር ብዬ ዘሃበሻም አውጥቶልኝ ነበር። ጹሑፌ አጭር ቆይታ ብቻ ነበር የነበረው። የፈራሁት እንሆ ደረሰ።
http://alltomypeople.blogspot.ch/2013/12/blog-post_2578.html
እኔ እንደሚገባኝ በአደራ ጠበቂው በአቶ አንዱዓለም አራጌ ውስጥ በፍጹም ሁኔታ አንድነት ፓርቲውአለ። በአንድነት ማዕከላዊ አመራር ውስጥ አቶ አንዱአለም ግን……. ቀደም ባለው ጊዜም በክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ውስጥ በፍጹም ሁኔታ አንድነት ነበር። በአንድነት ማዕከላዊ አመራር ውስጥ ወ/ት ብርቱካን ሜዴቅሳ ግን … በተመሳሳይ ብቃት፤ በሙሉዑ ተቀባይነት፤ የህዝብ ፍቅር የነበራቸው ሁለቱምየአንድነት ወጣቶች የነፃነት ቀንበጦች ላይ አንድነት የወስደው ተመሳሳይ እርምጃ ግን አልተመቸኝም።- አንጀቴንም አቃጠለው። ይህቺ እናት ሀገር ኢትዮጵያ ወጣቶቻና ሴት ልጆቿ መቼ ይሆን ቦታቸውን አግኝተው በብቃታቸው፤ በእርግጠኝነታቸው፤ በመሆን መቻላቸው፤ በሙቅና ትኩስ ፍላጎታቸው ትራስነት ከዚህ የመከራ ፍዳ የሚታደጉዋት። ወጣትነት እኮ ገዢ መሬት ላይ ያለ አጥቂ ሰራዊት ማለት ነበር። ወኔውም ልቡም ላለው። ማሸነፍ ማለት ወጣትነት ነው ለ እኔ። በመንፈስም በአካልም።
…. ዘመኑም ይሄዳል
እየለቀሙ ማፈስስ … እያፈሰሱ መልቀም …
ዕጣውም ይፈሳል – ጣጣው ይጎፍራል …..
ወጣቶቹ ለሚከፍሉት መስዋዕትን መታጋያ መድረካቸውን የሚያፈናቅል ተግባር ፊታውራሪ ሂደት እስር ላይ እያሉ ይፈጸማል። ይህ ጥቁር የታሪካችን ጠበሳ በወጣት የፖለቲካ መሪዎቻችን ላይ የተሰነዘረ የተስፋችን ጥቃት ነው። ያማል። የሚጎረበጥ – የጓጎለ ጎብዳዳ – ገጠመኝ። ዛሬ ላይ ሆነን የሰሞኑን ጉሽ ነገር ስንለካ፤ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ከኃላፊነቷ ላይ ሆና ብትሆን ኖሮ፤ ሚዛን ያለው ምላሽ በተሰጠው ነበር። ኢትዮጵያዊነትን በፈተነው ጠቀራማ ዘመቻ ላይ የግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የድርሻዋን ትውጣ እንደ ነበረ አልጠራጠረም። ግልጽ አቋምም ትወስድ ነበር። የጌጣችን ፈርጥ ሚስጢር እሷ ውስጥ ነበርና። ምክንያቱም ከነፃነት በላይ ትርጉም ያለው መንፈስ ሊኖር ከቶ አይችልም። የሰብዕናና የማንነት ምንዛሬ ህልውና ነጻነት!። ነፃነት ያለው ህዝብ በራስ የመተማመን መንፈሱ ሙሉዑ ነው። የትም ቦታ፤ በዬትኛውም ጊዜ፤ ማናቸውንም ፈተና የሞቋቋምና በእራስ እንደ ራስ ሆኖ የሚያቆም ዓውራ እሴቱ ነፃነት ብቻ ነውና። ስለሆነም ለአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማናቸውም ፈተና ከሀገሩ ሉዕላዊነት በታች እንጂ በላይ ሊሆን ከቶ አይችልም። ሀገር አለኝ ማለት የግጥምጥሞሽ ቃል አይደለም። የመኖር አለመኖር ህግ እንጂ ….
በሌላ ሀገር ቅኛ አለመገዛት እኮ ቃላት ሊገልጸው – ሊተነትነው – ሊፈትሽው የማይችል ረቂቅ መንፈስ ነው።አብነቱ አይደለም ለእኛ ዓለምን የናኘ ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ለነፃነት ያበቃ በኽረ ጉዳይ ነውና። ከዚህ አንፃር የክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ከፖለቲካ መድረክነት መገለል ጉዳቱ ለዛሬም – ለነገም ነው …. ሚስጢሩ ለሚገለጽላቸው …. በሌላ በኩል ትውልድ ከቶውንም ሊተካው የማይችለው የአፍሪካ የቅኔ ልዑሉ፣ ፓን እፍሪካኒስቱ፣ የሃያሲው፤ የመምህሩ፤ የጸሐፊው፤ የገጣሚው የብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን በህይወት አለመኖርም … ሌላው የልባችን ውጋት ነው። አጅሬ ቢኖር፣ እሱ ቢኖር እንዲህ ያለ ታሪክን ጨለመ የሚያለብስ ዘመቻ፤ ሆነ ድፍረትም ፈጽሞ አይታሰብም ነበር። በአንዲት ዘላላ ቅኔዊ ስንኝ አመጣጥኖ፤ አቻችሎ ቀጥ ያደርገው ነበር። የብዕሩ ደም ፈውስና መዳህኒት ነበርና … እሱም እንደ ብርቴ የኢትዮጵዊነት ልዩ ፈርጥ ቅመም ነበረውና አምላከ – ቅብዕ።
አሁን ወደ ቀደመው እንደ አቨው … አዎን! ወያኔ በህዝባዊ ፍቅር ተወዳድረው ያሸንፉኛል የሚላቸውን ወጣት የነፃነት አርበኞችን በነፃነት ትግሉ ማዕዶት አስርጎ ባስገባቸው አባሎቹ አማካኝነት እዬለቀመ ያሰራል፤ አቶ ሂደት ደግሞ መንገዱን ተከትሎ መስዋዕትነታቸውን አፈር ድሜ አስግጦ፤ ለዘር ሳያበቃ የበሬ ግንባር የምታክል የጉልማ መሬት ሳያስቀር ለሌላ አዲስ ሂደት አዲስ አመራር ይመርጣል፤ ይሾማል …. ይሸልማል፤ የድርጅቱ ዋነኛ ዓላማ ተስፋ — ቆራጭነትን ሰንቆ እሱን ያዬ፤ እሷን ያያ እያለ መቀጣጫ ያደርጋል … ቲያትሩ … ድራማው ይሄው ነው የፍታውራሪ ሂደት … ቁስለት!
„አንዱአለም የሰላም ታጋይ እንጂ አሸባሪ አይደለም“ በዬሀገሮች የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች መሪ መፈክር ነበር። „መንገድ በስሙ ይሰዬም“ ሌላው የህዝበ – ጉባኤ ድምጽ ነበር …. በቃ ይሄው ነው? … ማገዶነት ብቻ። የሰላማዊ ትግልን የሚያስከፍለውን መስዋዕትነት የሚከፍሉ ጀግኖች አሉን፤“ እያሉ በመሰዋዕትነቱ እምነት ጥለው ትግሉን የሚያግዙ፣ የሚረዱም ወንድሞችና እህቶች በርካታ ናቸው። ምልክታቸውን አንዱአለምን አድርገው። … ከአዲሱ መጸሐፉ ውስጥም ጥቅሶችን እያወጡ መንገዳችን ይሄ ነው የሚሉም ወገኖች አሉ። አሁን ይህን መርዶ ሲሰሙ ከቶ ምን ብለው ይሆን? አቶ ሂደት ካስመረጠው አዲሱ ዝርዝር ውስጥ እስረኛው፣ የሰላም መርህ አራማጁ እሩቅ አሳቢው አቶ አንዱአለም የለም። አይገርምም?! በውስጡ እያለ በሩን አቶ ሂደት ቀረቀረበት። …. እና ይሄው ነው በቃ?! … ድራማው ይህ ነው … ማለት ነው። አቶ ሂደት በቦታው ሌላ ሰው አስመርጦበታል። ቢፈታ የተሰዋለትን ፓርቲውን ትቶ ከቶ ዬት እንዲሄድ ነው የተፈረደበት … ስቃይ – የመንፈስ!
መቼም ይህ ሂድት የሚባል አንጀተ ደንዳና ርህራሄ የለውም … ለሁለት ምክትል ቦታ ከነበረው ምን አለ አንዱ ቦታ እንኳን ለመንፈሱ ደህንነት፤ ለፈኖቹ ሲል እንኳን ክፍት አድርጎ ቢጠብቀው … ለምን ሁለት አስፈላጊ እንደሆነ ባይገባኝም …. መቼም አቶ ሂደት መተዛዘን ነግ ለእኔ ቢል ጥሩ ነበር።
ሌላው በአቶ ሂደት የተገረምኩት ደግሞ የአዲሱ የአንድነት አመራር አካላት ሙህራንና በእድሜያቸውም ከ60% በላይ በወጣቶች ተገነባ የሚባለው ጉድ ነው። …. የትኞቹ ናቸው ወጣቶች ፕሬዚዳንት የሆኑት? …. ቲያትር ነው … ። እርግጥ ነው እኔም እማምንበት አንድ መርህ አለ …. ወጣትና ነበር የፖለቲካ ተመራጮች የሂደት ተከታታይነት ማደረግ ይጠበቃል …. እርሾ።
… ይህም ቢሆን በኢጂነር ግዛቸው ከነባሩ አመራር ስላልነበሩ ክፍተት አለው። የሆነ ሆኖ አሁንም እዛው ከአዛውንታት ላይ ነው ያለው የመወሰን፤ የመምራት ቁልፉ …. የዛሬው ትውልድ እጅግ የቀደመና የሰለጠነ ሆኖ ሳለ ግን ተፈራ …. ለምን?! አባቴ መዳህኒተ ዓለም ይወቀው። ….ተከታዩ ካቴና የሚጠብቀው ደግሞ ማን ይሆን? …. አቶ ሂደት ልጆቹን ለካቴና እያመቻቸ ያቀብልና ለአዲስ ትወና ይዘጋጃል …. መስራች – ልዩ – ማሟያ እያለ …
ደጃችዝማች ሂደት ካቴና ላይ ለሚገኙ አካሎቹ መንፈስ ቢያንስ ተቆርቋሪ ቢሆን መልካም ነው። ለቤተሰቦቹም ይሰብ። „ነግረንህ ነበር አስታውሰንህ ነበር“ የሚሉ አይጠፉም እንዲህ አይነት ተርጓሚ አጥብቆ የሚሻ ገጠመኝ ሲታይ። ኃላፊነት ያለው ተግባር ቢፈጽም መልካም ነው። የአሁኑ ሆናል። አይተናል ሰምተናል … ይብቃኝ መሰልየተቋጠረን መግል ለማፍሰስ፤
እርገት። የቀድሞው የአንድነት ሊቀመንበር ዶር/ ነጋሶ ጊዳዳ በቃኝ ማለታቸውን በአውንታዊነትና በቅንነት ማዬት ይገባል። በወያኔ ሥርዓት ውስጥ የነባራቸውን የሥም ቦታ በፈቃዳቸው ለቀቁ፤ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ህዝብም ይቅርታ ጠዬቁ፤ ከጎጥ አስተሳሰብ ወጥትው የአንድነት ኃይሉ ቤተሰብ ሆኑ፤ እኔኑ እሰሩኝ ወጣቶቼን ልቀቁ ብለው የትክክለኛ እረኝነትን አብነትም አሳዩን። አሁንም ከዕድሚያቸው ጋር ሊመጥን የሚችል እርምጃ ወሰዱ። ስለሆነም የሚወስዷቸው እርምጃዎች ሁሉበምሳሌነት ሊያሰመሰግናቸው ይገባል እላለሁ እኔ፡ እንዲያውም እንዲህ የሚል ጠፍቶ ነው ተተኪው አዲስ ወጣት ትውልድ አቅሙን የሚተረጉምበት መድረክ ያጣው – የዘመንም ግጭት ደልቶት የምናዬው።
ትንሽ ብትክትክ አልኩ መሰል፤ ያለተመቸኝንም የተመቸኝም አዘናንቄ የምለውን አልኩ።ቸር እንሰንብት።
Sunday, 12 January 2014
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ እና የኢትዮጵያ ምህዳር ጋዜጣ አዘጋጆች ለውሣኔ ተቀጠሩ
በህገመንግስቱ ላይ ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት፣ የህዝብን ሃሳብ በማናወጥ እና “ጨፍጫፊ” በማለት የመንግስትን መልካም ስሙን በማጥፋት የተከሰሰው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በመከላከያ ማስረጃነት ያቀረበው የቢቢሲ ዶክመንተሪ ፊልም፣ የቢቢሲ ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ሲል ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለውሣኔ ቀጥሯል፡፡
ተከሳሹ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ያዘጋጀው ነው በሚል በመከላከያ ማስረጃነት የቀረበው የድምጽ ምስል ዶክመንተሪ ፊልም በእርግጥም የቢቢሲ ስለመሆኑ ጥያቄ በማስነሳቱ ከጣቢያው ሃላፊዎች ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ቀደም ባለው ቀጠሮ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው፡፡ ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት የተከሳሽ ጠበቃ ለፍ/ቤት እንዳስረዱት፤ ማረጋገጫውን ለማግኘት ከቢቢሲ ሃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህኛው ቀጠሮ ሊደርስላቸው ባለመቻሉ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ማስረጃ ይከላከሉልኛል ያላቸውን የሰው ምስክሮች ለፍ/ቤቱ ከማሰማቱም በተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ መከራከሩ ይታወሳል፡፡
ለፍ/ቤቱ ካቀረባቸው የመከላከያ የሰነድ ማስረጃዎች መካከልም 4 ገጽ ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሠመጉ) ሪፖርት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “ኢትዮጵያን አመጽ አያሰጋትም” ሲሉ የሠጡት ቃለ ምልልስ፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንዲሁም ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ በፎከስ ኦን አፍሪካ ያሠራጨውና ፍ/ቤቱ ማረጋገጫ የጠየቀበት ዘገባ ይገኙበታል፡፡ ተከሣሹ ባቀረባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች ላይ አስተያየቱን የሰጠውን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የቀረቡት ማስረጃዎች ከክሱ ፍሬ ሃሳብ ጋር ግንኙት የላቸውም ብሎ የተከራከረ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ሣይቀበለው ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ያለውን አጠቃላይ አስተያየት በቀጣዩ ቀጠሮ ለማቅረብ ፍ/ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሳሽን የቢቢሲ ዘገባ ማረጋገጫ ለመቀበልና የአቃቤ ህግን አጠቃላይ የማስረጃ አስተያየት ሠምቶ ውሣኔ ለመስጠት ለየካቲት 5 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ሐዋሣ በሚገኘው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፤ የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲ የ300ሺህ ብር የፍትሃ ብሔር ክስ ያቀረበባቸው የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ አሳታሚና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ደግነው እንዲሁም ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤት ቀርበው የቃል ክርክር ካደረጉ በኋላ፣ የፍ/ቤቱን ውሣኔ ለመስማት ለጥር 20 ቀን 2006 ተቀጥረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፍ/ቤቱን ሂደት ለመከታተልና ስለዘገባው ማብራሪያ ለመስጠት ወደ ሃዋሣ በሄደበት ወቅት የትራፊክ አደጋ የደረሰበት ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ስለ አደጋው ፖሊስ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ቃሉን የተቀበለ ሲሆን፤ እስካሁን ግን ክስ እንዳልተመሠረተ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
Thursday, 9 January 2014
የመንግስት የፕሬስ ተቋማት የግል መጽሄቶችን በጽንፈኝነት ፈረጁ
የመንግስት የፕሬስ ተቋማት የግል መጽሄቶችን በጽንፈኝነት ፈረጁ
መንግስታዊዎቹ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና በሕግ በፈረሰ ድርጅት ስም የሚጠቀመው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ አስጠንተነዋል ባሉት ጥናት መሰረት በአገር ውስጥ ከሚታሙት መጽሄቶች መካከል አዲስ ጉዳይ፣ፋክት፣ሎሚ፣ቆንጆ፣ጃና፣እንቁ እና ሊያ የተባሉ መጽሔቶች ጽንፈኛ ፖለቲካ አራማጆች መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።
አዲስዘመን ጋዜጣ በረቡዕ ታህሳስ 30 ቀን 2006 ዕትሙ መጽሔቶቹ በብዙ ባህርያቸው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት መሆናቸው፣ በተሳሳቱ መረጃዎች ሕዝቡ በስርኣቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ ዘገባዎችን ያቀርባሉ ብሏል፡፡
በጥናቱ መጽሔቶቹ የመንግስትን ኃላፊዎች የግል ስብዕና እንደሚነኩ፣የአመጽ ጥሪዎችን እንደሚያሰሙ፣ሽብርተኝነትን እንደሚያበረታቱ፣የፖለቲካ ስርዓቱን እንደሚያጨልሙ፣ኢኮኖሚ ዕድገቱን እንደሚክዱ፣ህገመንግስቱን እንደሚጥሱ በዝርዝር አቅርቧል፡፡
መንግስት መጽሄቶችን በጽንፈኝነት በመፈረጅ ምናልባትም ከ2007 ምርጫ በፊት እንዲዘጉ ሊያደርግ ይችላል ሲል አንድ ያነጋገርነው ጋዜጠኛ ተናግሯል።
"መንግስት ምንም አይነት እርሱ ከሚያራምደው አጀንዳ ውጭ የተለየ ድምጽ መስማት አይፈልግም" የሚለው ጋዜጠኛውም፣ መጽሄቶችን በተለያዩ መንገዶች በመፈረጅ ከገበያ ለማውጣት ያሰበ ይመስላል ሲል አክሎአል።
ኢትዮጵያ የፕሬስ መብቶችን በማፈንና ጋዜጠኞችን በማሰር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ ውብሸት ታየ፣ የሱፍ ጌታቸውና ሌሎችም ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ መታሰራቸው ይታወቃል። ከምርጫ 97 በሁዋላ እጅግ ዝነኛ ጋዜጣ ሆነ የወጣው ፍትህ ጋዜጣም በመንግስት ጫና ከገበያ እንዲወጣ ተደርጓል። በጋዜጣው ላይ ሲሰሩ የነበሩት ታዋቂ ጋዜጠኞችም በተለያዩ ክሶች ሲዋከቡ ቆይተዋል።
Saturday, 4 January 2014
Thursday, 2 January 2014
ቴዲ አፍሮና የቢራው ፖለቲካ
በጋዜጠኛ ስህተት የወጣች አንዲት ጽሁፍ ምክንያት 18 ሺህ ፊርማ በኢንተርኔት መሰበሰቡን ሰማን። ጽሁፉን ያሳተመው መጽሄት ስህተቱን አረመ። ይቅርታም ጠየቀ። ዘመቻው ግን እንደቀጠለ ነው። ቴዲ አፍሮ ይንን እንዳልተናገረ መግለጫ ቢሰጥም ጉዳዩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም። ከቶውንም አንድነታችንን የማይፈልጉ ምእራባውያን ጭምር ይህችን ምክንያት በመያዝ ጉዳዩን ማረገብ ጀመሩ። አንድ የዳች ጋዜጣ አጼ ምኒሊክን ከሂትለር ጋር አመሳስሎ በመጻፍ ጋዜጣውን በዚህ ሳምንት አሰራጭቷል! ያለ አንዳች መረጃ። “ለነጮች እጄን አልሰጥም!” ብሎ አድዋ ላይ ስላዋረዳቸው ምኒሊክን ለማንቋሸሽ ምንም መረጃ አያስፈልጋቸውም።
እልፍነሽ ቀኖ የተባለች የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ በአንድ ወቅት በለቀቀችው ነጠላ ዜማ ምክንያት ማእከላዊ እስር ቤት ታስራ ነበር። ምርመራውን የሚያካሂዱት ሰዎች በመጀመርያ የዘፈኑ ግጥም ወደ አማርኛ እንዲተረጎም አደረጉ። በግጥሙ ምንም አይነት የወንጀል ነገር ሲያጡ ግጥሙ “የህግ ትርጉም ይደረግለት” ሲሉ አዘዙ። የህግ ትርጉሙም ብዙ ስላላስኬዳቸው ለግጥሙ የፖለቲካ ትርጉም እንዲሰጠው አደረጉና ሙዚቀኛዋን “ጥፋተኛ ነሽ” ሲሉ ከሰሱ። የፖለቲካ ትርጉሙ “ይህን ያለችው እንዲህ ለማለት ነው…” ከማለት ተነስቶ አቀንቃኝዋ በልቧ አስባው ይሆናል የሚለውንም ያካተተ ነበር። በኢትዮጵያ “የፍትህ ሰዎች” የምናስበውንም ያውቁ ኖሯል።
የበደሌ ቢራ አድማ ጠሪዎች ቴዲ አፍሮ በልቡ ያሰበውን የማንበብ ሃይል እንዳላቸው አናውቅም። እሱ ግን የተባለውን ነገር እንዳልተናገረ ገልጾላቸዋል።
አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያከሄዱት ጦርነት “ቅዱስ ጦርነት ነው” ወይንም “አይደለም” የሚለውን ሙግት ለግዜው ወደጎን እንተወው። ምክንያቱም የዚህ ውይይት ውጤጥ የኦሮሞ ህዝብ አሁን ላለበት ችግር የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም። የህሊና አይኖቹን ክፍት አድርጎ ለሚመለከት ሁሉ፤ የዛሬው የኦሮሞ ህዝብ ችግር የበዴሌ ቢራን ከመጠጣት እና ካለመጠጣት የላቀ ነው። ለነገሩ እንጂ 90 በመቶ የሚሆነው የኦሮሞ ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና፤ ኑሮውም ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ የበደሌ ቢራን የመጠጣት አቅሙም ሆነ እድሉ የለውም። የዚህ ዘመቻ መሪ ተዋንያን የሆነው ጃዋር መሃመድ እንደነገረን ከሆነ ደግሞ 90 በመቶው የኦሮሞ ህዝብ የሙስሊም እምነት ተከታይ ነው። በሙስሊም አልኮል “ሃራም” ነው።
“እስር ቤቱ ሁሉ ኦሮምኛን ይናገራል!” ያለው ማን ነበር? አዎ! የስርዓቱ ቁንጮ የነበረው ስዬ አብርሃ ነው። ስዬ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከርቸሌ ታስረን የነበርን ጋዜጠኞች የእነ ኦቦ ባይራን ጉዳይ እያነሳን በኦነግ ስም በግፍ ለታሰሩት ስንጮህ የዝሆን ጆሮ ነበር የሰጠን። አቶ ስዬ አብርሃ አይኑ የተከፈተውና ጆሮው ኦሮምኛን መስማት የጀመረው እጆቹ የኋሊት ታስረው ቃሊቲ ሲወርድ ነበር። በእርግጥ ማየት ማመን ነው። ያየውንና የሰማውን በመመስከሩ ሊመሰገን ይገባዋል። ልብ በሉ። እስረኛው ሳይሆን እስር ቤቱ ነው ኦሮምኛ እየተናገረ ያለው።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ሰሞኑን በለቀቀው ዘገባ፤ በኦሮሞ ወገናችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን አስከፊ ስቃይ በድምጽና በምስል ጭምር አሰራጭቷል። ይህንን ስቃይ ለማስቆም የፌስቡክ ታጋዮቹ ስንት ሺህ ፊርማ እንዳሰባሰቡ አልነገሩንም። የበዴሌ ቢራን የኦሮሞ ህዝብ እንዳይጠጣ በ24 ሰዓታት ውስጥ 18 ሺ ፊርማ ተሰብስቧል ብለውናል።
እርግጥ ነው። “ሰብአዊ መብት ይከበር!” የሚል ዘመቻ ከመጀመር ይልቅ “ቢራ አትጠጡ!” ማለቱ ቀላል ሊሆን ይችላል። በምእራቡ አለም የሚመረተውን ሄነከን ቢራ ራሳቸው እየተጎነጩ ይህንን ቀጭን ትእዛዝ ሲያስተላልፉ ግን በዚያ ትልቅ ህዝብ ላይ እያሾፉበት መሆኑን የዘነጉት ይመስላል።
የኦሮሞ ልሂቃን ግራ ያጋቡኛል። ይህን ስል ያለምክንያት አይደለም። በአባ ጅፋር ግዛት ተወልጄ በኦሮሞ ባህል ታንጼ ነው ያደግኩት። በደሙ ብቻ ‘ኦሮሞ ነኝ’ እያለ ከሚመጻደቀው ይልቅ የኦሮሞን ህዝብ ማንነት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ቋንቋው፣ ባህሉና ስነልቦናው ውስጡ ሰርጎ ሳይገባ በደሙ ብቻ ራሱን እየለካ ከህልም እና ከቅዠት አለም ውስጥ ገብቶ የኋሊት ከሚራመደው በተሻለ መንገድ። … እናም አንድ የኦሮሞ ህዝብ አውቃለሁ። በቋንቋው፣ በባህሉና በታሪኩ የሚኮራ ህዝብ። ታታሪና ሰራተኛ ህዝብ። ከሌላው ጋር ተዋልዶና ተከባብሮ በፍቅር አብሮ የሚኖር ህዝብ። የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር በደም ተሳስሯል። ሃቁ ይህ ነው። ግና ፖለቲከኞቹ ከዚህ ህዝብ በሁለት ሺህ ማይልስ ርቀው በምእራቡ አለም በሚሰሩት ስራ ይህንን ትልቅ ህዝብ እጅግ ትንሽ የሚያደርግ መሆኑን ያስተዋሉት አይመስለኝም።
በቅርቡ ሳውዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የጸመችውን ግፍ ለመቃወም በአለም ዙርያ ያለ ኢትዮጵያዊ በጋራ በሚጮህበት ወቅት አንድ እንግዳ ክስተት በኢንተርኔት ላይ ወጥቶ አየን። “ሳውዲ አረቢያ ኦሮሞን አትግደሉ፣ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም፣ ኦሮሞ ወንጀለኛ አይደለም።” የሚል መፈክር የሚያሰሙ ሰዎች ለብቻቸው ሰልፍ ወጡ። እነዚህ ሰዎች የተሰለፉት “ኦሮሞን አትንኩ። ሌሎቹ ግን ወንጀለኞች ስለሆኑ ይገባቸዋል” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነበር። መቼም ከማንም ሰብአዊ ፍጡር እንዲህ አይነት ኢ-ሰብአዊ አባባል አይጠበቅም። ድርጊታቸው ያሳፍራል። አንገትም ያስደፋል። ይህ አሳፋሪ ድርጊት እኔን እንዲህ ካሸማቀቀኝ፤ አፈር ስንፈጭ ያደግነው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሮ የኦሮሞ ልጆች ቢያዩት ምን ሊሉ እንደሚችሉ በምናቤ እስል ነበር። በዚያ ትልቅ ሕዝብ ስም አደባባይ ወጥተው፣ ተግባራቸው ግን ማስተዋል የተሳነው ትንሽ ህዝብ ነበር። ያንን ኩሩ ህዝብ እንዲህ … እንዲህ እያሉ ሊያሳንሱት አየን።
እ.ኤ.አ. በ1998 ገደማ አቶ ዳዊት ዮሃንስ በሆላንድ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። ከስብሰባው መሃል አንድ ሰው ከመቅጽበት ተነስቶ ‘ለኦቦ ነጋሶ ጊዳዳ የሚያደርሱልኝ ጥብቅ መልእክት አለኝ’ አለ። ስብሰባውን የሚመራው አቶ ዳዊት ዮሃንስም ሰውዬው ተነስቶ መልእክቱን እንዲናገር ፈቀደለት። ሰውየው ከመቀመጫው ተበሳ።
“ፊንፊኔ መሃል ላይ ያለው የምኒሊክ ሃውልት በአስቸኳይ እንዲነሳ ይንገሩልን!” አለ ፊቱን ቅጭም አድርጎ በኩራት እየተናገረ። በስብሰባው የነበርን ሰዎች ግን ለተናጋሪው አፈርን። ያሳፈረን ይህንን መልእክት ማስተላለፉ አልነበረም። ሰውየው ሊናገር ከመቀመጫው ሲነሳ ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ያነሳል ብለን ገምተን ስለነበር እንጂ። ‘ሰዎች በዘራቸው (በኦሮሞንታቸው) ብቻ የሚታሰሩት፣ የሚሰቃዩትና የሚገደሉት እስከመቼ ነው?’ የሚል መልእክት ነበር የጠበቅነው። ምክንያቱም ወቅቱ በቁጥር 20 ሺህ የሚደርስ የኦሮሞ ተወላጆች የጦር ካምፕ እስረኛ እንዲሆን ካደረጉ በኋላ፤ የኦነግ መሪዎች በባሌ ሳይሆን በቦሌ እየተሸኙ የወጡበት ሰሞን ነበር። የኦነግ መሪዎች ከህወሃት ጋር በጋራ መስርተውት የነበረውን ቻርተር ረግጠው በመውጣታቸው ምክንያት ኦሮሞው ወገናችን የህይወት መስዋእትነት ጭምር ይከፍል የነበረበት ወቅት።
ዳዊት ዮሃንስም አግባብ ያለው ጥያቄ መሆኑን ከተናገረ በኋላ መልእክቱን ለርእሰ-ብሄሩ እንደሚያደርስ ቃል ገብቶ ሄደ። መልእክቱን ለዶ/ር ነጋሶ ያድርስ፤ አያድርስ የታወቀ ነገር የለም። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በዚያን ወቅት የሃገሪቱ ርዕሰ-ብሄር ነበሩ። እንኳንና የተባለውን መልእክት ሊያስፈጽሙ፤ እሳቸውም የዛ ስርዓት ሰለባ ሆነው አየን።
የአጼውን ሃውልት ግን ዛሬ በባቡር ሃዲድ ስራ ምክንያት ከነበረበት ስፍራ እንዲነሳ አድርገውታል።
የተዛባ ታሪክ ይዘን፣ ጥላቻን ብቻ በምናባችን አርግዘን የት እንደምንደርስ አላውቅም። አሁንም በመፍትሄው ላይ ሳይሆን በችግሮቹ ላይ ተወጥረናል። የምኒሊክ ሃውልት ተነሳም አልተነሳ እንደ እንስሳ ለሚታደነው የኦሮሞ ህዝብ ምን ፋይዳ አለው? “በእስር ያሉ ወገኖቼ ይፈቱ!” ለማለት እንኳን ሞራል ሳይኖረን አእምሯችንን በአፈ-ታሪክ ብቻ ወጥረን አንዲት ኢንች እንኳን ወደፊት መራመድ እንዳልቻልን ለምን አናስተውልም?
አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን ግዛት አንድነት ለማስፋፋት ባደረጉት ጦርነት ወንጀል ፈጽመው ከሆነ አጽማቸው ወጥቶ ለፍርድ ይቅረብ ነው የምትሉት? ወይንስ ይህ ትውልድ የዚያ ወንጀል ውርስ አለበት? ውርስ ካለበትስ ማን ነው ወራሹ? አማራው? ጉራጌው ወይንስ ኦሮሞው? እንደ ዘረኞች፣ ደም መለካት ካለብን እኚህ መሪ ከአማራም፣ ከኦሮሞም፣ ከጉራጌም ይወለዳሉ። ጠለቅ ብለን ከሄድን ደግሞ ራስ ጎበና ዳጬን በዚያ ስእል ውስጥ እናያለን። ምእራብ እና ደቡብ ኢትዮጵያን በሃይል የያዙና ያስገበሩ የአጼው የጦር መሪ። ራስ ጎበናን ልንጠላቸው እንችል ይሆናል። ኦሮሞነታቸውን ግን ልንክደው አንችልም። የወንጀል ውርስ በተዋረድ (guilt by association) ውስጥ ከገባን የኦሮሞን ህዝብም በአእምሯችን ለፈጠርነው ወንጀል ወራሽ ልናደርገው ነው።
የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” አልበም የሚያሞግሰው ኢትዮጵያን ከወራሪ ጠላት የታደጉትን ጀግኖች ነው። እነ ፊታውራሪ ሃብተጎርጊስ ዲነግዴን እና እነ ባልቻ አባ ነፍሶ። ቴዲ አፍሮ ለነዚህ ጀግኖች ባያቀነቅንላቸውም ከታሪክ መዝገብ ላይ ልንፍቃቸው አንችልም። የታሪክ ተመራማሪዎች ስለነዚህ ጀግኖች የጻፉት አፈ-ታሪክ ወይንም ድርሰት አይደለም። በጀግኖቹ የምንኮራው በዘራቸው ሳይሆን የሰሩት ገድል ነው። በ’ጥቁሩ ሰው’ የተመራው ይህ የጸረ-ቅኝ ግዛት ገድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካና ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ሊዋጥላችሁ የሚገባ እውነታ ነው። በዚያ ገድል የሚያፍሩ ካሉ የራሳቸው ጉዳይ። መላው የአፍሪካ ህዝብ ግን ይኮራበታል። የአለም ጥቁር ህዝብም ሲያስታውሳቸው ይኖራል።
ዘር እየቆጠርን ከሄድን ብዙ የሚጎረብጡ ነገሮችን ልናነሳ ነው። በግዛት ማስፋፋቱ ሂደት ግን አንድ ሃቅ አለ። ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ህልቀ መሳፍርት ኢትዮጵያዊ አልቋል። ይህ ደግሞ የድንበር መስፋፋት፤ እድገት እና ስልጣኔ ይዞት የሚመጣው ችግር እንጂ አንድን ህዝብ ለመጨረስ ጥናት ተደርጎ የተሰራ እንዳልሆነ ታሪኩን ከስር መሰረቱ ማየቱ ይበጃል። ችግሩ በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በአያሌ ሃገሮች እንደተከሰተ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። በ17ኛው ክፍለዘመን የተከሰተው የኢንዱስትሪ አብዮት ሳብያ እንኳን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት የማይተናነስ እልቂት ነበር።
አጼ ምኒሊክን ከጀርመኑ ኦቶ ቮን ቢስማርክ ጋር የሚያመሳስሉ ምሁራንም አሉ። እርግጥ ነው ጀርመን አሁን የያዘችውን ግዛት ቅርጽ እንድትይዝ ያደረገው ፕሩሲያዊው ቢስማርክ ነው። ቢስማርክ የጀርመንን አንድ ታላቅ ኤምፓየር ለመፍጠር አንባገነን፣ ሃይለኛና ጦረኛ መሆን ነበረበት። ታዲያ ይህችን ሃያል ሃገር በመመስረቱ ጀርመኖች አልጠሉትም። ይልቁንም የጀግንነት ስያሜ ለግሰውታል። አያሌ የመታሰቢያ ሃውልቶችንም አቁመውለታል።
ቢስማርክ የህግ ምሁር ነበር። አጼ ምኒሊክ ግን መደበኛም ሆነ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ሰው አልነበሩም። ከታሪክ እንደምንረዳው በአጼ ልብነድንግል ዘመነ መንግስት፤ የግራኝ አህመድ ወረራን ተከትሎ የነበረውን መከፋፈልና መተላለቅ ለማስቆም መሪዎች ተነሱ። ሃገርን አንድ የማድረጉን ትግል አጼ ዮሃንስ ጀመሩት፣ አጼ ቴዎድሮስ ቀጠሉበት ከዚያም እምዬ ምኒሊክ ተረከቡት።
አጼ ምኒሊክ ለአመታት በኦነግ ሰዎች ተወግዘዋል። ውግዘቱ አሁንም እታገልለታለው የሚሉትን ህዝብ ችግር ሲፈታው አለየንም። በ1991 ከህወሃት ጋር ጋብቻ ፈጽመው የምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሲገቡ ይናገሩት የነበረውን ሁሉ ረሱት። ከቶውንም ያነሱት የነበረው የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጉዳይ ሳይሆን የስልጣን ጥያቄ ለመሆኑን አረጋገጡልን። የሽግግር መንግስቱን ቻርተር ሲያጸድቁ “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” የሚለውንም ሳያውቁ ዘንግተውት ነበር። ከገዢው ፓርቲ ጋር የጀመሩት ግዚያዊ ጋብቻ በፍቺ ሲጠናቅቅ የምኒሊክ ጠላትነት መፈክራቸውን እንደገና አነሱት።
የዘር ፖለቲካው ስካር ሞቅ ብሎ በነበረበት በዚያን ወቅት እንደቀልድ ይነገር የነበረ አንድ ቁም ነገር አለ። አንድ የምግብ ቤት በር ላይ በላቲን ፊደል “አማራ መግባት ክልክል ነው!” የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል። የጽሁፉ ትርጉም ያልገባው አንድ የአማራ ተወላጅ ጎራ ብሎ ምግብ አዘዘ። አስተናጋጆቹ የሰውየው ድፍረት አስደነገጣቸው። ባለስልጣን ስለመሰላቸው አስተናገደዱት። ዳግም እንዳይመለስም እጥፍ ዋጋ አስከፈሉት። ሰውየው በድጋሚ ሲመጣ ሶስት እጥፍ አስከፈሉት። በሌላ ግዜ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር መጥቶ ምግብ አዘዘ። ከተስተናገደ በኋላም አራት እጥፍ ቢል አቀረቡለት። በዚህ ግዜ ቲፕም ጨምሮ ሰጣቸው። የሆቴሉ ባለቤት በነጋታው “አማራ መግባት ክልክል ነው!” የሚለውን ጽሁፍ አንስቶ “ኦሮሞ መግባት ክልክል ነው!” በሚል ቀየረው።
በአሁኑ ዘመን ከበድ አለ እንጂ፣ ሰዎችን በጎሳ አደራጅቶ ከማሳደም የቀለለ ትግል የለም። ደም ከውሃ ይወፍራል እንዲሉ፤ ሰዎች በጋራ የሚጋሩትን ነገር እያነሱ ስነልቦናዊ ዘመቻ ማድረግ ስኬት ሊኖረው ይችላል። ዘለቄታ ግን አይኖረውም። የዘር ፖለቲካ ልክ እንደ ስካር ነው። ይሞቃል ከዚያም ይበርዳል። በርግጥ በሞቅታ ግዜ የሚፈጠረው አደጋ ቀላል ላይሆን ይችላል። እ.ኤ.አ. በ1993 በምስራቅና በምእራብ ኢትዮጵያ የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ለዚህ ዋቢ ነው። የኦነግ ልሂቃን የ19ኛውን ክፍለ ዘመን ጉዳይ እየደጋገሙ ያነሱልናል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በራሳቸው እጅ የተፈጸመው ግድያ ግን በብሄራዊ ቴሌቭዥን ጭምር እንድናየው ተደርጓል። ነብሰ-ጡር ሴቶች በጩቤ ሆዳቸውን እየተሰነጠቁ ሲገደሉ አየን። ነብስ ያላወቁ ሕጻናትና የ90 አመት አዛውንት ጭምር ከተራራ ላይ እየተወረወሩ ሲጣሉም የአይን ምስክሮች ነን። እነዚህ ሰዎች የምናስታውሰው ይህን በመሰለ ወንጀል ብቻ አይደለም። ድርጊቱ የቂምና የቁርሾ አሻራ ጥሎ አልፏል።
ይህ ሁሉ በደል በዘመናችን ተፈጸመ። በዳዮቹ ግን አሁንም በቀልን አርግዘው ይጓዛሉ።
የበደሌ ቢራን አለመጠጣት የኦሮሞን ችግር የሚፈታ ከሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቢራውን መጠጣት ያቁም። የአኖሌን ሃውልት መሰራት ለኦሮሞ ህዝብ ፍትህ የሚያመጣ ከሆነ ደግሞ፤ ሃውልቱ በየከተማው ይገንባ። ግና ይህ ሃውልት ለመጭው ትውልድ ጥሎት የሚያልፈው ቂምና በቀልን እንጂ፤ ለሚታገሉለት ህዝብ የፍትህ ጥያቄ ዋስትናው ምን እንደሆነ ልንረዳው አልቻልንም። አሁን ያለው ትውልድ ያልፋል። ከዚህ ትውልድ በኋላ ለሚወለዱት ልጆች ጥለንላቸው የምናልፈው ቅርስ ጥላቻ፣ ቂም እና በቀል ብቻ ይሆናል።
ከዘመናችን ታላቅ ሰው ከኔልሰን ማንዴላ አንድ ነገር እንማር። ማንዴላ የደቡብ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን የአለምን ፖለቲካ የለወጠ የፖለቲካ ነብይ ነው። ይህንን ሲያደርግ የፖለቲካ ፎርሙላ አልነበረውም። ክፉን ነገር በበጎ ለማሸነፍ ወሰነ። ጥላቻን በፍቅር ለወጠ። ልክ እንደ ክርስቶስ፣ የበደሉትን ሁሉ ይቅር ብሎ በፍቅር አሸነፋቸው። ታሪክ ሰርቶ አለፈ። ስሙም ከመቃብር በላይ ለዘልአለሙ ይኖራል።
Subscribe to:
Posts (Atom)



