Wednesday, 26 November 2014

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አመራሩ ድብደባ እንደተፈጸመበት ገለፁ።

አንድ ወር የትግል መርሃ ግብር ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችና ህዝባዊ የለውጥ ንቅናቄዎችን በገዥው ፓርቲ አፈና እና ማስፈራሪያ እንደማይቆም ትብብሩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ህዳር 7/2007 ዓ.ም የትብብሩ ህዝባዊ የአደባባይ ስብሰባ በኃይል መበተኑን፣ ይህንኑ አስመልክቶ ህዳር 7/2007 ዓ.ም ለሰማያዊ ፓርቲ ማስጠንቀቂያ መጻፉን እና ለህዳር 21 ለሚደረገው ስብሰባ የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ደብዳቤ በፖስታና በአካል ቢላክለትም ማሳወቂያ ክፍሉ አልቀበልም ማለቱን የገለጸው መግለጫው ስርዓቱ የትብብሩን የትግል መርሃ ግብር ለማስቆም እየጣረ መሆኑን ገልጾአል፡፡ በተጨማሪም የትብብሩ አንድ አባል እና ትብብሩ ህዳር 21/2007 ዓ.ም የሚያደርገውን የአደባባይ ስብሰባ የሚያስተባብረው መኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ የሆኑትን አቶ ኑሪ ሙደሲር ላይ የድብደባ ወንጀል እንደተፈጸመባቸው አመራሩ ገልጸዋል፡፡ ትብብሩ በዛሬው ዕለት ‹‹ማስፈራራትና አፈና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችንና ሠላማዊ ሕዝባዊ የለውጥ ንቅናቄዎችን አይቀለብስም›› በሚል በሰጠው መግለጫ የተገኙት አቶ ኑሪ ሙደሲር ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ወከባ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ ኑሪ ‹‹መኪናችን ገጨህብን ባሉ 10 ሰዎች ነው የተደበደብኩት፡፡ ከአሁን ቀደምም ፖሊሶች ምንም አይነት ችግር ሳላደርስ ገጨህብን ብለው አዋክበውኛል፡፡ ሰሞኑን መኪናዬን ቢሰብሩብኝም በስህተት የተመታ መስሎኝ ነበር፡፡ አሁን ከደበደቡኝ መካከል ተክለኃይማኖት አካባቢ የሚገኙ ካድሬዎችና ደንብ አስከባሪዎች ይገኙበታል፡፡ መጀመሪያ ላይ ፖሊሶች ‹ቢገጭስ እንዴት 10 ሆናችሁ አንድ ሰው ትደበደርባላችሁ?› ካሉ በኋላ እንደገና ካድሬዎች መሆናቸውን ሲያውቁ እነሱን ትተው እኔን ይወቅሳሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር መሆኑን ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ህዳር 21/2007 ለሚደረገው የአደባባይ ስብሰባ በአካልም ሆነ በፖስታ ደብዳቤ ቢላክም የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ባለመቀበሉ የትብብሩ ደብዳቤ በፋክስ እንዲደርሰው እንደተደረገ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በፋክስ የተላከውን ደብዳቤ አልቀበል ካለ የትብብሩ አመራሮች በጋራ ደብዳቤውን ለማድረስ እንደሚሄዱ፣ የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ይህንም አልቀበልም ካለ ሁነቱን በቪዲዮና በፎቶ በመቅረጽ ለህዝብ በማሳወቅ ስብሰባውን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በሂደቱም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል እንደተዘጋጁ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡

Friday, 14 November 2014

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፖሊስ ጣቢያዎችን እንዲሰሩ ተጠየቁ

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በየ አካባቢያቸው ለሚሰሩት አዳዲስ ፖሊስ ጣቢያዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ መጠየቃቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ በየ አካባቢው የሚገኙት የፖሊስ ጣቢያዎች ነዋሪዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ በየ ቤታቸው ደብዳቤና የገንዘብ መክፈያ ቅጽ እየሰጡ ሲሆን ነዋሪዎቹ ገንዘብ እንዲከፍሉ የተጠየቁበትን ቅጽ ሳይሞሉ መመለስ አይችሉም ተብሏል፡፡ ደብዳቤው ላይ ባለው የፖሊስ ጣቢያው ስልክ ቁጥር ደውለን ያነጋገርናቸውና ስማቸውን ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆኑ አንድ የፖሊስ አባል ‹‹ህዝቡን ለምን ፖሊስ ጣቢያ እንዲሰራ ታስገድዳላችሁ?›› በሚል ላነሳነላቸው ጥያቄ ‹‹ህዝቡኮ ራሱ ነው ሴት ልጆቻችን በሰላም መግባት አልቻሉም እያለ ያለው፡፡ ፖሊስ የህዝብ እስከሆነ ድረስ ህዝብ ፖሊስ ጣቢያ ቢያሰራ ምን ችግር አለው? ህዝቡ አልከፍልም ካለ ሊቀር ይችላል፡፡ እናንተ ግን ይህን እንደጥያቄ የምታነሱት ስብሰባው ላይ ስላልነበራችሁ ነው፡፡›› ብለውናል፡፡ ከወራት በፊት ‹‹ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ›› በሚል አደረጃጀት ህዝቡ በየቤቱና ከጎረቤት ጋር 1ለ5 በመደራጀት ከፖሊስ ጋር ግንኙነት እንዲኖረው የሚያዝ ህግ መውጣቱና ነዋሪዎቹንም ማደራጀት መጀመሩን ነገረ ኢትዮጵያ መዘገቧ ይታወቃል፡፡

Wednesday, 12 November 2014

የፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ልዩ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ ተነሱ፡፡

የፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ልዩ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ ተነሱ፡፡ አቶ አሰፋ የተነሱት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡ በአቶ ኃይለ ማርያም ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ አቶ አሰፋ ከኃላፊነት የተነሱበትን ምክንያት ያልጠቀሰ ሲሆን፣ አቶ አሰፋም በምን ምክንያት እንደተነሱ እንዳላወቁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ወደፊት የሚተገበሩ አዳዲስ ፕሮግራሞችን እየቀረፅኩ ነበር፤›› በማለት ከኃላፊነት መነሳታቸው ያላሰቡትና ያልጠበቁት እንደሆነ አቶ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ደብዳቤው በጥቅሉ፣ አቶ አሰፋ ከኅዳር 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናውን ገልጿል፡፡ በሥራ አፈጻጸምም ሆነ በሙስና እንዳልተገመገሙ አቶ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸው፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አዲስ የሥራ መደብ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ መጻፉን ተናግረዋል፡፡ የሸካ ዞን፣ የኪ ወረዳ፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ የነበሩት አቶ አሰፋ፣ የክልሉ ፀረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነርና የደቡብ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአምስት ዓመታት የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡ አቶ አሰፋ የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ ከመሆናቸው በፊት፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሆነውም ሠርተዋል፡፡ አቶ አሰፋ የፍትሕ ሚኒስቴርን ለሦስት ዓመታት ከመሩ በኋላ ከቦታው ተነስተው የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ ሆነው ተሰይመዋል፡፡ አቶ አሰፋ ላለፉት ስድስት ዓመታት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስንና በቅርቡ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ሲያማክሩ ቆይተዋል፡፡

Tuesday, 11 November 2014

ግልጽ ደብዳቤ ”ለጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ : ከታሳሪ ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስታችንን ያክብሩ! ሠላም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!? እንዴት ነዎት? ያስታውሱ ከሆነ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢከፊሉ የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች ‘ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ’ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎትን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሕገ መንግስታችንን ድንጋጌዎች እየጣሱ ነውና እርስዎም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 74/13/ መሠረት ሕገ መንስቱን የማስከበርና የማክበር ግዴታ ስላለብዎት ሕገ መንግስቱን ያክብሩ” በማለት አንዲት አጭር ደብዳቤ ፅፈንልዎት ነበር፡፡ ድንገት በተለያዩ ምክንያቶች የጻፍንልዎትን ደብዳቤ ካላነበቡት ወይም ማስታወስ ካልቻሉ ዛሬ ይሄን ማስታወሻ ስለምንፅፍልዎት ግለሰቦች አንድ ሌላ ማስታወሻ እንስጥዎ፡ ከ6ወራት በፊት /በሚያዚያ 2006 ዓ.ም/ ሶስት ጋዜጠኞችንና ስድስት ጦማሪያንን ‘ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል ጠርጥሬያችኋለሁ’ በማለት መንግስትዎ ልማታዊ ርምጃ (አብዮታዊ ርምጃ እንደሚባለው) ወስዶ ነበር፡፡ እኛም የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች የዚህ ‘ልማታዊ ርምጃ’ ሰለባ የሆንን ግለሰቦች ነን፡፡በርግጥ ከሁለት ዓመታት በፊት ‘ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስቱን’ ያስከብሩልን በማለት ጥያቄ ያቀረብንልዎት ግለሰቦች ‘ከ6 ወራትበፊት ሕገ መንግስቱን ለመናድ ሞክራችኋል’ በማለት መንግስትዎ ሲያስረን ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ጠይቀን ሕገ መንግስቱን ለመናድ በመሞከር ወንጀል ተጠርጥረን ስንታሰር እስሩ በጣም ግራ አጋብቶን ነበር፡፡በዚህ ያልቆመው መንግስትዎ ክሱን ‘ሕብረተሰቡንና ሀገሪቱን ለማሸበር አቅዳችኋል ሞክራችኋል አሲራችኋል…’ በማለት ወደ ‘ሽብርተኝነት’ያሳደገው ሲሆን እርስዎም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳብዎትን ሲሰጡ ስለተመለከትንዎ ትንሽ ቅሬታ ይዘን መጣን፡፡ በቅድሚያ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በትንሹ ብናስረዳዎት ቅሬታችንን ለመረዳት ያስችልዎታልና አንዳንድ ጉዳዮችን እንንገርዎት፡፡ ይሄን ማስታወሻ በምንፅፍልዎት ወቅት ከታሰርን ከ 200 ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን፣ነገር ግንጉዳያችን ገና በቅድመ ክስ (Pre Trial) የክርክር ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም መንግስትዎ እንኳን ለእኛ ለተከሳሾች ለከሳሽ አካልም ግልፅ ያልሆነ ክስ በማቅረቡ ነው፡፡ ይሄንንም ስንል ልትፈፅሙት ነበር የተባለው ‘የሽብርተኝነት ድርጊት’ ሳይጠቀስ ‘በቃ የሽብርተኝነት ድርጊት ልትፈፅሙ ነበር’ በማለት በጨበጣ ስለመጣብን ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንግዲህ የብዙ ድብደባ፣ ዛቻ እና ስድብ ሰለባዎች ከሆንን በኋላምየቀረበው ይሄ ክስ ነው ከ6 ወራት በኋላም ተከሳሾች ከሳሾቻችንምሳንረዳው በየቀጠሮው እየታሸ ነው የሚገኘው፡፡ ‘የተፋጠነ ፍትህ’ ሕገ መንግስትዊ መብት ነውና የተፋጠነ ፍትህ ይሰጠን፣ እርስዎምይሄን ሕገ መንግስታዊ መብት ያክብሩ እያልንዎት አይደለም ‘ሕገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ሕገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ’በማለት ‘ጥፋት የሚያሳምን’ ( አንዱ የዚህ ደብዳቤ ጸሃፌ ጦማሪ ጥፋት ብሎ አንዲፈርም የተገደደው ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለህገመንግስቱ ይከበር ማለቴ ጥፋት ነው ብሎ መሆኑ መንግስትዎን መልክ ግልጽ አድርጎ ያሳያል) መንግስት አለዎትና ይህ ጥያቄ አንደሚበዛብዎትእናውቃለን፡፡ ይልቁንም ቀላልና ግልፅ ቅሬታን ነው ይዘን የመጣነው፡፡ ይሄውም የኢፌድሪ ሕገ መንግስትበአንቀፅ 20/3/ ላይ ‘የተከሠሡ ሰዎች[…] በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር[…]መብት አላቸው::’ በማለት የደነገገ ሲሆን፣ ይሄንን ሕገ መንግስታዊ መብትም ማንኛውም የመንግስት አካል እንዲሁም ግለሰብ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እርስዎና መንግስትዎም በተደጋጋሚ ‘ሕገ መንግስቱ ሳይሸራረፍ እናስከብራለን’ ይላሉና ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የምታውቁት ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ከታሰርን ወዲህ ስለእኛ የእስር ጉዳይ በተጠየቁባቸውጊዜያት ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ ‘ፍርድዎትን’ በተደጋጋሚ ሲሰጡ ታዝበናል፡፡ እናስረዳዎ፡- ሐምሌ 12/2006 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣሚ መግለጫ ላይ ስለእኛ እስር ጉዳይ ለቀረበልዎት ጥያቄ ሲመልሱ፡- ‘ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የሽብር ሰንሰለት ውስጥ አንዴከገቡ በኋላ ብሎገር ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ ማለት ዋጋ የለውም’ በማለት ብዙ ነገሮችን ተናገሩ፡፡ ይሔውልዎት ስህተትዎ፡- 1. የክሳችን ዋነኛ ጭብጥ በሃገርውስጥ ‘የሽብርተኛ ድርጅት በማቋቋም ‘የሽብርተኝነት’ ተግባራትን ለመፈጸም አሲረዋል፡ አቅደዋል… የሚል እንጂ፣ እርስዎም እንደሚሉት ‘ሰንሰለት’ ምናምን አይደለም፣ 2. እሺ አሸባሪዎችም ይበሉን፣ነገር ግን ሕገ መንግስቱ እንደሚደነግገው በፍርድ ቤት ‘ጥፋተኝነታችን’ እስሚረጋገጥ ቢጠብቁስ ምናለበት? ይህ የሚያመለክተው እርስዎም እንደ ማእከላዊ መርማሪዎች ነፃ ሆኖ የመገመት (presumption of innocence) መብታችንን እያከበሩልን እንዳይደለ ነው፡፡ ይሄ ነገር የሆነው በድንገት ሊሆን ይችላል ብለንዝም ብንልም እርስዎ ግን በድጋሚ ጥቅምት 6/2007 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባል ለቀረበልዎ ጥያቄሲመልሱ፡- “የብሎገር ጭምብልአጥልቆና በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተሸሽጎ ከተከሳሽነት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ሽብርተኝነትን መዋጋታችን ይቀጥላል…” እያሉ እርስዎ ያሉትን የብሎገር ጭምብል አውልቀውና ተሸሸጉበት ያሉትን የጋዜጠኝነት ሙያመሸሸጊያ አፍርሰው ባንዴ ‘የአሸባሪነት’ ካባ ደረቡልን፡፡ ክቡር ጥቅላይ ሚኒስቴር፣ እያልን ያለነው የአንድ ሰው ‘አሸባሪነት/ወንጀለኝነት’ የሚረጋገጠው በፍርድ ቤት እንደሆነ ሕገ መንግስቱ ደንግጎ እያለ፣ እርስዎ ግን ነፃ ሆኖ የመገመት መብታችን ወደ ጎን ብለው እንደ ከሳሽም እንደፈራጅም በመሆን ‘አሸባሪዎች’… እያሉን ይገኛሉ ነው፡፡ ምናልባት ‘ስራ አስፈጻሚው ከሳሽ ነውና እኔም የስራ አስፈጻሚው አካል መሪ ስለሆንኩ የፈለኩትን አስተያየት የመስጠት መብት አለኝ’ ብለው ከሆነ፣ ሕገ መንግስቱን የማክበር ጉዳይ ‘ርስዎን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ላይ የተጣለ ግዴታነው፡፡ እርስዎ ‘L’e’tat, c’est moi’ ይሉት አይነት የራስ ግምት ውስጥዎ ከሌለ በስተቀር እንዲህ በግልፅ እየጠየቅንዎት ‘ሕገ መንግስትቱን አላከብርም’ በማለት ገና ዋነኛ ክርክሩ እንኳንያ ልተጀመረ ክስን (ዋነኛ ክርክር ካለው) መሠረት በማድረግ ከዚህ በኋላ እኛን ‘አሸባሪዎች’ አይሉንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ይህን ተመሳሳይ ምላሽ “በእርግጠኝነት አሸባሪ ናቸው” በሚል ቃና ለቢቢሲ ለኢንቢሲ ለመሳሰሉት አለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማትም መስጠትዎን ሰምተናል፡፡ ሌላው ልናስታውስዎ የምንፈልገው ጉዳይ እንደኛ አይነት የተራገበ( በሰፊው በታወቀ የአደባባይ)የፍርድ ጉዳይ ([un] popular case) ላይ የመንግስት አካላት አስተያየት (say) ያለውን ተፅእኖ እንዲያስቡት ነው፡፡እርስዎ በምክር ቤት ቀርበው የአሸባሪነት ፍርድ ከበየኑብን (አሁን እያደረጉት እንዳሉት) ፍርድ ቤትም ሆነ ሌሎች የመንግስትዎ አካላትምን ሊያስቡ እንደሚችሉ አስተውለውታልን?! ይሄን ሁሉ ስንልዎ እንዲያው ሕጉን ያክብሩልን ለማለት ያክል ነው እንጅ፣ ከሽብርተኝነትጋር የሚያገናኘን ቅንጣት ያክል እውነት /A segment of fact/ እንደሌለና የሰው ልጆች መልካምና ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸውከመመኘትና ለአገራችን ያገባናል ከማለት ያለፈ ሕይወትም ፍላጎትም እንደሌለን እኛም እናውቀዋለን እርስዎና መንግስትዎም ያውቁታል፡፡ነገር ግን ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ጨዋታውን በግድ ካልተጫወታችሁ ተብለናልና እየተጫወትን ነው፡፡ የአሁኑ ጥያቄያችን ግን በጣም ቀላል ነው፣ ጨዋታው ገና በደንብ እንኳን ሳይጀመር ውጤቱን እይወስኑት ነው፡፡ እርስዎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ደረጃ በወጡ ሰሞን አብዛኞች የዚህ ማስታወሻፀሃፊዎች መጠነኛ ለውጥና ማሻሻዎች ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ሰንቀን “The First 100 Days” ወዘተ እያልን ብዙ ጠብቀንዎት ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በሚበልጥ ግዜ እንደተመለከትንዎ ግን ተስፋችን ፍሬ ሊያፈራልን አልቻለም፡፡ አሁንም አዲስ ተስፋ ሰንቀን ግን ፡-“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እባክዎትን ሕገ መንግስቱን ያክብሩ! የእኛንም መብት ያክብሩልን” እንላለን፡፡ ‘’የብሎገር ካልሲ አድርጎ፣ የጋዜጠኝነት ጫማ ተጫምቶ የሽብረተኝነት ሰንሰለት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሕገ መንግስቱን ያክብሩልኝ ማለት ዋጋ የለውም!’’በማለት ተስፋችን ዋጋ እንደማያሳጡት ተስፋ አለን፡፡ ከአክብሮት ጋር ጦማርያን ጋዜጠኞች ዘላለም ክብረት ኤዶም ካሳዬ ናትናኤል ፈለቀ ተስፋለው ወ/የስ በፍቃዱ ሃይሉ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ አጥናፍ ብርሃኔ አቤል ዋበላ ማህሌት ፋንታሁን

Tuesday, 4 November 2014

ጦማርያንና ጋዜጠኞቹ ለሳምንት ቀጠሮ ተሰጠባቸው

ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለ10ኛ ጊዜ ችሎት የቀረቡት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሶስቱ ጋዜጠኞች ለሳምንት (ህዳር 3/2007 ዓ.ም) ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ ዛሬ በጦማርያንና በጋዜጠኞቹ ቀደም ሲል የቀረበውን የክስ ማሻሻያ አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ምርመራው አላለቀም በሚል ምክንያት አጭር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዛሬው ችሎት ላይ ከተሰየሙት ዳኞች መካከል ሁለቱ አዲሶች በመሆናቸው ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃ አምሃ መኮንን ገልጸዋል፡፡ ዳኞች ብቻ ሳይሆን ችሎት ክፍሉም በመቀየሩ ክፍሉ ጠባብ ነው በሚል፣ የተከሳሽ ቤተሰቦችና ጋዜጠኞች ችሎት መግባት አለመቻላቸውም ታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በነገው ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተከሳሾች ዋስትና ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን አቶ አምሃ ጨምረው አስረድተዋል፡፡ በተከሳሾች በኩል ደግሞ፣ ሁለቱ ሴት ተከሳሾች (ኤዶም ካሳዬ እና ማህሌት ፋንታሁን) በቃሊቲ ማረሚያ ላይ ያነሱትን የመብት ጥሰት አቤቱታ በተመለከተ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በቀጣይ ቀጠሮ ድጋሚ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች በቀን ለ10 ደቂቃ ብቻ ስማቸው ቀድሞ በተመዘገቡ ሰዎች ብቻ እየተጎበኙ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡