Monday, 29 September 2014
የታጋይ አንደርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በአውሮፓ ህብረት ምክርቤት ኮሚሽን ውይይት ተደረገበት፤ በአስቸኮይ እንዲፈታም ጠይቀዋል።
ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌ በአምባገነኑ ወያኔ እጅ ወድቆ መሰቃየት ከጀመረ 3 ወራት አልፈዋል። ባለፉት ቀናት የአውሮፓ ህብረት የሰበአዊ መብት ም/ቤት በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ውይይት አደርገዋል ። አንዳርጋቸው የፖለቲካ እስረኛ እና ለዲሞክራሲ፣ ለነጻነት፣ ለመልካም አስተዳደር እና ሰበአዊ መብት መከበር የሚታገል የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር ሲሆን ባስቸኮይ ተለቆ ወደ እንግሊዝ እንዲመለስ ኮሚሸነር ተናግረዋል፡፡የተከበሩ አና ጎሜዝ አንዳርጋቸው ብቻ አይደለም በርካታ ኢትዮጵያኖች ታስረዋል ብሎግ ዘጠኝ፣ ጋዜጠኞች፤ ፖለቲከኞች ሁሉም ካለ ምንም ምክንያት መፈታት አለባቸው። የኢትዮጵያን ፓርላማ ባለፈው ሂጄ አይቸዋለሁ በጣም የሚገርም ነው የፖለቲካ እስረኛ ሳይሆን ሽብርተኞች ናቸው ያሉን ሲሉ ከአንድ መንግስት የማይጠበቅ ነው። እስክንድር ነጋ ሽብርተኛ ሳይሆን አለም አቀፍ የብእር ተሸላሚ ነው። ብሎግ 9 ጸሃፊያን፣ ጦማሪያን ናቸው። አንዳርጋቸው ጽጌ የፍትህ ታጋይ ነው። ታዲያ እንዴት ነው የኢትዮጵያ መንግስት ህግን የሚተረጉመው ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በሁለት ወር ውስጥ ይህን ጉዳይና የኢትዮጵያን ሰበአዊ መብት በተመለከተ እና የአንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ የሚመለከት ኮሚቴ እንዲሰየም እና እንደገና እንደሚወያዩበት የወሰኑ ሲሆን የአቶ አንዳርጋቸውን በተመለከተ አሳሳቢ በመሆኑ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በመሆኑ ለብቻ በሚቀጥሉት እናየዋለን ሲሉ ዘግተዋል።
በዚሁ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ ቀርበው አሁንም የተለመደ ማስተባበያ ሰጥተዋል። እኛ ምንም አይነት ህግ አልጣስንም ብለዋል።
Friday, 19 September 2014
በህወሓት አገዛዝ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጅምላ ግድያ በጽኑ እናወግዛለን!!!
የአገራችን የኢትዮጵያን በትረ ሥልጣን በጠመንጃ ኃይል የተቆጣጠረው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየወሰደ ያለውን እሥራትና ግድያ አጠናክሮ መቀጠሉን የሚያጋልጡ ማስረጃዎች በየጊዜው ከራሱ ከአገዛዙ እየሾለኩ በመውጣት ላይ ናቸው።
መስከረም 5 ቀን 2007 ዓም በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን በምስል ተደግፎ የቀረበው በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከነዚህ ማስረጃዎች አንዱ ነው ።
የወያኔን አገዛዝ ይቃወማሉ የተባሉና በኦጋዴን ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ጋር ንኪኪ አላቸው የተባሉ እነዚያ የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ ምስኪን ዜጎች አስከሬን መሬት ለመሬት እየተጎተተ አንድ ቦታ እንዲከማች ሲደረግ፤ አስከሬኑን ለመሰብሰብ ከታዘዙት የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ የገዛ ወንድሙ አስከሬን ከሚጎተተው መሃል እንደነበረ መስማት ህሊናን የሚሰቀጥጥና የወያኔ የጭካኔ እርምጃ አቻ የሌለው ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው።
በደርግ ዘመን ቤተሰብ የተገደለበትን ሰው አስከሬን ለማግኘት የጥይት ዋጋ ለመክፈል ይገደድ ነበር በማለት ሥርዓቱን በነጋ በጠባ የሚወነጅል አገዛዝ ከሚወነጅላቸው ሥርዓት በባሰ በኦጋዴን የገደለውን ንጹህ ዜጋ አስከሬን የገዛ ወንድሙ መሬት ለመሬት እንዲጎትተው አድርጓል። በዚህም ህወሓት በሰብዓዊነት ላይ ከቀደምቶቹ ሁሉ የከፋ የሚሰቀጥጥ ወንጀል ፈጽሟል። ቀደም ሲል በበደኖ፤ በአርሲ፤ በአርባ ጉጉ፤ በሃዋሳ ፤ በጋምቤላ እና ድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ነዋሪዎች ላይ በወያኔ ልዩ ትዕዛዝ ተመሳሳይ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። ይህ ሁሉ ወንጀል እየተፈጸመብን አስከዛሬ ወያኔን በጫንቃችን ተሸክመን ለመኖር የተገደድነው እነዚሁ ጥቂት ዘረኞች ሕዝባችንን በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት በመከፋፈላቸው አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ሲጠቃ ሌላው በዝምታ የሚመለከትበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው።
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ይህንን አረመኔያዊ እርምጃ አጥብቆ ያወግዛል። ጊዜው ሲደርስ የዚህ ወንጀል ፈፃሚዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብሎ ያምናል። ስለሆነም ወያኔ ሕዝባችንን አቅም ለማሳጣት ላለፉት 23 አመታት በኅብረተሰባችን መካከል የገነባውን የጥርጣሬና የጥላቻ ግንብ በመናድ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኦጋዴንና በሌሎች የአገራችን ክፍሎች ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰቆቃና እልቂት ለማስቆም እንዲችሉ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
ኦጋዴን ውስጥ ለፈሰሰው የንጽሃን ደምና በሰብዓዊነት ላይ እየተፈጸመ ላለው ወንጀል ተጠያቂው ሥልጣንን በኃይል የሙጥኝ በማለት በአገርና በሕዝብ ሃብት ዘረፋ ላይ የተሰማራው ጥቂት የህወሃት አመራር መሆኑ አያጠያይቅም። ይህንን ወንጀለኛ ቡድን ለፍርድ ለማቅረብ ንቅናቄዓችን ግንቦት 7 የሚያደርገውን ሁለገብ ትግል ለፍትህ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ የቆመ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲቀላቀል በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ቀርቦለታል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Sunday, 7 September 2014
የኢህአዴግ አባላት በድርጅታቸው ላይ ጥያቄዎችን ማንሳት ቀጥለዋል
በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለከተሞች በመካሄድ ላይ ባለው የኢህአዴግ አባላት ስብሰባ ፣ አባላቱ ዛሬም በርካታ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ መዋላቸውን ከውስጥ ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ በአባላቱ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል፡- ” የኢትዮጵና የኤርትራ ህዝቦች የማይነጣጠሉ የአንድ ሃገር ዜጎች ሆነው ሳለ በመሪዎች አለመግባባትና ሽኩቻ በመለያየታቸው እስከዛሬ ድረስ እየተላቀሱ ይገኛሉ፤ ይህም የሆነው በኢህአዴግም አስተዋፆ ጭምር ነው፤ አሁንም ቢሆን ከኛ ጋር መስማማት ከፈለጉ በራችን ክፍት ነው የምትሉት ከልባችሁ ነወይ?” የሚለው ጥያቄ ሰፊ ሰአት ወስዶ ማከራከሩ ታውቋል።
በሃይማት አክራሪነት ጉዳይ ለተነሱት ጥያቄዎች ደግሞ ” ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ሰልፍ በጠራበት ጊዜ ሰልፈኛው መስኪድ አካባቢ ሲደርስ ሙሉ ለሙሉ ለጸሎት ወደ መስኪድ እንደገባ አረጋግጠናል፤ ስለሆነም
” መንግስት ሁሉንም ሚዲያዎች እንደጥፋተኛ ቆጥሮ ጋዜጦችና መጽሔቶችን እንዳለ ከገበያ ማስወጣቱ እኛ አባሎቹ የኢህአዴግን ክፍተት የምናውቅበት መንገድ ተዘግቷል፤ ኢህአዴግ ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል እፈጥራለሁ እያለ በአንፃሩ ግን የስራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ዜጎች በአባልነት ላይ የተመረኮዘ ለምን ይሆናል? በታችኛው ህብረተሰብ አካባቢ በብልሹ አሰራር ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ሙስና የሰሩና በህዝቡ የተገለሉ ሰዎች ተሸፍነው ወደ ላይ ሲወጡ ሹመት ይደረብላቸዋል ይህ ተገቢ ነወይ?” የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።
የአዲስ አበባ የመሬት ወረራ ጉዳይም ሰፊ አጀንዳ የነበረ ሲሆን፣ ኢህአዴግ በሰላማዊና ጠንካራ ተቃዋሚዎች ላይ የያዘው አቋምም ትችት አዘል ጥያቄ አስነስቶበታል።
የዛሬውን የፕላዝማ ውይይት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው መርተውታል።
ትናንት ከሰአት በሁዋላ በነበረው የውይይት ጊዜ ደግሞ ” ኢህአዴግ ለሃገሪቱ ስጋት ብሎ ከለያቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛ ያላቸው የሃይማኖት አክራሪነት ወይም ጽንፈኝነት እና የመልካም አስተዳደር እጦት ቢሆኑም፣ የ ኑሮ ውድነቱ በስጋትነት ሊካተት ይገባል” የሚል አስተያየት ቀርቧል።
የደመወዝ ጭማሪው አርኪ አለመሆኑና እንዳውም የበለጠ ህዝቡንና የመንግስት ሰራተኛውን ለችግር መዳረጉም በአባላቱ ተነስቷል።
ሰልጣኞቹን በሚሰለጥኑበት ቦታ ጥያቄዎች ሲነሱ እዚያው በህዋሳቸው በሰልጣኞቹ እንዲመለስ በማሰብ በህዋስ ማደራጀት መጀመሩን፣ ሰልጣኞቹ የመድረኩን የፕሮፓጋንዳ ገለፃ ብዙ ትኩረት ሳይሰጡ የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ሲደርስ ግን በንቃት ጥያቄ የሚያነሱ ሲሆን፣ አንዳንዳ ጥያቄዎችን ከውይይሩ ጋር ግንኙነት የላቸውም ወይም ጥያቄውን ወደ ኋላ ላይ ማንሳት ትችላላችሁ በሚል እንደሚታለፉ የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ የግንቦት 7 ድርጅት አጀንዳ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ አባላት ዘንድ ግንቦት 7 ከውጭ መንግስታት ጋር በማበር በሀገር አብዮት እንዲነሳ እየሰራ ነው ሲሉ ሌሎች አባላት ደግሞ ግንቦት 7 አሸባሪ ከተባለ ለምን የአሜሪካ መንግስት አሳልፎ አይሰጥም? እናንተ እንደምትሉት አሸባሪ ቢሆን ኖሮ ያስሩዋቸው ነበር ብለው ተከራክረዋል፡፡ አወያዮቹም ከአሸባሪዎች ጋር መገናኘት የለባችሁም፣በሀገር የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች አብረው እየሰሩ እንደሆነ ለአባላቱ የገለጹ ሲሆን ንክኪ እንዳይኖራችሁ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በኢህአዴግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ግምገማ መነሻ፣ በቅርቡ ኢህአዴግ መዳከሙን የተመለከተ ግምገማ ከተደረሰ በሁዋላ ነው። ይህን ተከትሎ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ፖሊሶች፣ የህግ ባለሙያዎች በመንግስት ፖሊሲ ዙሪያ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በስልጠናው ላይ የተነሱትን ጥያቄዎች የኢህአዴግ አባላት እንዲመክቷቸው በሚል እየተሰጠ ያለው ስልጠና ያልተጠበቁ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ፣ ከፍተኛ አመራሮችን ሳይቀር በእጅጉ ማስገረሙን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
“እዚህ የምናደርገው ስብሰባ በኢሳት ይዘገባል ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ? ” በሚል አመራሩ እየተነጋገረበት መሆኑንም ታውቋል።
ብአዴንም መረጃዎች እየወጡ ተቸግረናል በሚል ትናንት በጀመረው ግምገማ ማንም ሰው ሞባይል ስልኮችን ይዞ እንዳይገባ ከልክሏል።
Subscribe to:
Posts (Atom)