Saturday, 16 August 2014

“አሸባሪነት” በወያኔ አገዛዝ ሥር ባለችው ኢትዮጵያ

በአገራችን፣ በወያኔ አገዛዝ መደበኛ ትርጉማቸውን ከሳቱ በርካታ ቃላት መካከል “የሽብር ድርጊት“ እና ”አሸባሪ“ የሚሉት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ሰፊ ተቀባይነት ያለው የአሸባሪ ትርጉም “የሽብር ድርጊቶችን የሚፈጽም ሰው ወይም ድርጅት” ማለት ነው። “የሽብር ድርጊቶች” የሚባሉት ደግሞ የተለመዱ ጥቃቶችን ሳይሆን የሀይማኖት፣ የፓለቲካ ወይም የርዕዮተዓለም ግብ ለማሳካት ሲባል በሰዎች ላይ ፍርሀትን ለማንገስ፤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሱ አስከፊ ጥቃቶችን ነው። የሽብር ድርጊቶችን ሰላማዊውን ሕዝብ ጭዳ የሚያደርጉ በመሆኑ በጥብቅ ሊወገዙ ይገባል። ዓላማን በሽብር ድርጊቶች ማስፈፀም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። በወያኔ መዝገበ ቃላት ግን “ሽብርተኛ” እና “የሽብር ድርጊቶች” በዘፈቀደ የሚነገሩ ተራ ቃላት ሆነዋል። ስለአገራቸው እና ስለትውልድ የሚጨነቁ፤ ሀሳባቸው በነፃነት የሚያራምዱ፤ የወያኔን ፕሮፖጋንዳ እንደ በቀቀን የማይደግሙ ዜጎች “አሸባሪዎች” እየተባሉ ወደ እስር ቤቶች እየተወረወሩ ነው። ጋዜጠኞች፣ ጦማርተኞች፣ ፍጹም ሰላምተኛ አማኞች እና ሰላማዊ ፓለቲከኞች በሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዙ ናቸው። በአንፃሩ ደግሞ እውነተኛው አሸባሪ ህወሓት፣ የመንግሥትን ሥልጣን ይዞ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሸበሩን በስፋት ተያይዞታል። ህወሓት ዘረኛ ርዕዮተ ዓለሙን ለማስፈፀም ሲል ባለፉት ሠላሳ አምስት ዓመታት ውስጥ የፈፀማቸው የሽብር ድርጊቶች ተዘርዝረው አያልቁም። የህወሓት የሽብር ድርጊቶች ዓላማ የኢትዮጵያን ሕዝብ በፍርሀት አደንዝዞ መግዛት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ “አሸባሪ” የሚለውን ቃል ራሱ በማሸበሪያ መሣሪያነት እያዋለው ነው። ይህ የውስጥም የውጭም ታዛቢዎችን የሚያሳስት በመሆኑ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው። “የፀረ-ሽብር አዋጅ” የሚባለው ህገ-አልባነትን ህጋዊ ያደረገው ሰነድ የመንደር ካድሬዎች ሳይቀሩ አንድን ሰው በሽብርተኝነት “ጠርጥረው” ማሳሰርና ማስደብደብ አስችሏቸዋል። የአስተሳሰብ ድህነት ያጠቃቸው የህወሓት ካድሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ኃላፊነት የጎደላቸው ፓሊሶችም የፀረ-ሽብር ህጉን ጉልበታቸውን ማሳያ እና ተፎካካሪዎቻቸውን ማጥቂያ አድርገውታል። በፀረ-ሽብር ህጉ ተከስሰው ወህኒ የወረዱ ዜጎችን ያጤነ ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያ አገራችን በዚህ ህግ ሰበብ ምርጥ ዜጎቿን እያጣች እንደሆነ ይገነዘባል። በሽብርተኝነት ለመጠርጠር የሚያበቁ ምክንያቶች እጅግ አሳዛኝ ናቸው። ለካድሬ ሰበካ እውነተኛነት ጥርጣሬውን የገለፀ አስተዋይ ሰው መሆን ብቻውን እንኳን በሽብርተነት ያስጠረጥራል። በዚህም ምክንያት ነው በእውቀትም በአስተሳሰብም የበሰሉ ዜጎቻን በአሸባሪነት የመፈረጅ እድላቸው ከፍተኛ የሆነው። የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በርካታ የሀገራችን ምርጥ ዜጎች የዚህ የተዛነፈ ትርጓሜ ሰለባ ሆነዋል። ተስፋ የሚጣልባቸው በርካታ ወጣቶች በዚህ ህገ-ወጥ ህግ እና የተሳሳተ ትርጓሜ ምክንያት የወጣትነት እድሜዓቸውን በእስር ቤት እንዲያሳፉ ተገደዋል። ከዚያ የበዙት ደግሞ በቃሉ ተሸማቀው፤ በሚያስከፍለው ዋጋ ተሸብረው ራሳቸውን እንዲደብቁ ተደርገዋል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ምርጥ ዜጓቿ በአሸባሪነት ስም ወህኒ እየተወረወሩ ሲሰቃዩ ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል? እስከመቼ አስተዋይ፣ አርቆ አሳቢና አመዛዛኝ የሆኑ መሪዎቻችንን ለወያኔ ፋሽቶች እየገበርን እንኖራለን? ሀገራችን ይህን ኪሳራ የመሸከም አቅም አላት? ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔን ለማስወገድ የተሻለ ነው ብሎ ያመነበት የትግል ስልት – ሁለገብ የትግል ስልት ነው። በዚህ የትግል ስልት መሠረት ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሕዝባዊ አመጽ ተደጋግፈውና ተናበው መሄድ አለባቸው ብሎ ያምናል። ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአመቸውና በሚያምንበት መንገድ ለትግሉ አስተዋጽኦ የማበርከት እድል አለው። በዚህም መሠረት ለሀገር፣ ለትውልድ ድህንነት ዋጋ ለመክፈል እና ለገዛ ራሳችን ህሊና ታማኝ ለመሆን በወያኔ “አሸባሪ” ለመባል መድፈር የትግላችን አንዱ አካል አድርገን መቁጠር ይኖርብናል። በወያኔ “አሸባሪ” መባል የሚያሸማቅቅ ሳይሆን የሚያኮራ፤ ለታላቅ ኃላፊነት እና ሕዝባዊ አደራ በእጩነት የሚያቀርብ መሆኑን በራሳችንም በማኅበረሰባችንም ውስጥ ማስረጽ ይኖርብናል። “አሸባሪ” የሚለው ቃል በወያኔ ተግባር መሠረት ሲተረጎም “ለሀገርና ለትውልድ ደህነት የሚጨነቅ ምርጥ ዜጋ“ ማለት እንደሆነ ማስተማር ይገባናል። ወያኔ ወደ ሕዝብ የሚወረውረውን ጦር መልሰን ወደ ራሱ መወርወር ይኖርብናል። ወያኔ አሸባሪነት ዜጎችን ለማጥቂያ እያዋለው መሆኑ ተረድተን እኛ በዚህ ስያሜ መሸማቀቅ ሳይሆን፣ መኩራትና መልሰን ወያኔን ማሸማቀቅ ይኖርብናል። በውጭ አገራት እየተስፋፋ የመጣው የወያኔ ሹማምንትን የማሸማቀቅ ዘመቻ በኢትዮጵያ ውስጥም መጀመር ይኖርበታል። ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽ ሲቀናጁ ድላችንን ያፈጥናሉ። በወያኔ “አሸባሪ” መባል የመልካም ዜግነት ምስክርነት እንደሆነ በሙሉ ልባችን እንቀበል። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Thursday, 14 August 2014

የአዲስ አበባ መስተዳድር በቤቶች ግንባታ ዙሪያ ለምርጫ እንዲደርስ በሚል አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጠ

በ40 በ60 በሚባለው የቤቶች መርሃግብር የታቀፉ የዲያስፖራ አባላት ከቀጣዩዓመት ምርጫበፊት ቤት እንዲሰጣቸው የአዲስ አበባ መስተዳድር መመሪያመስጠቱ ታውቋል። ሆኖምየጠቅላላተመዝጋቢውንየቤትፍላጎትለመሸፈንበትንሹከ16 ዓመታትበላይጊዜን እንደሚወስድ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ኢንተር ፕራይዝ እስካሁን 13ሺህ 800 ቤቶችን በሰንጋተራ እና ቃሊቲ ክራውን ሆቴል በመሳሰሉ አካባቢዎች ላይ እየገነባ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ፣ እነዚህን ቤቶች እስከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ድረስ ለዕድለኞች ለማስተላለፍ ታቅዷል። የአስተዳደሩ ምንጮች እንደገለጹት ቤቶቹ ከቀጣይ ዓመት ምርጫ በፊት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው እንዲተላለፉ ከአስተዳደሩ መመሪያ ተሰጥቷል። ሆኖም ለ40 በ60 የቤቶች ፕሮግራም የተመዘገበው ጠቅላላ ሕዝብ ቁጥር 164 ሺህ 779 ያህልሲሆንአስተዳደሩግን በዓመትከ10 ሺህቤቶችበላይቤቶችን የመገንባት አቅም ባለመፍጠሩ የተመዘገቡትን ብቻ ለማዳረስከ16 ዓመታት በላይ ጊዜን እንደሚፈልግ የአስተዳደሩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከዛሬ ነገ የመኖሪያ ቤት ባለቤት አስቆራጭ ዜና ነው ብለዋል፡፡ በ20/80 በተለምዶኮንዶሚኒየምፕሮግራምየምርጫ 97ን መቃረብ ታሳቢ አድርጎ ሲጀመርከ 350ሺ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ መኖሪያ ቤት እፈልጋለሁ ብሎ መመዝገቡን ያስታወሱትምንጮቹ ፣ ፕሮግራሙ 10 ዓመታት ያህል ቆይቶ መመለስ የቻለው ግን 100 ሺ በታች ቤት ፈላጊዎችን ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡በዚህ መረጃ መሠረት የጠቅላላ ተመዝጋቢውን ፍላጎት ለሟሟላት ተጨማሪ ከ20 ዓመታት በላይ ጊዜ ንእንደሚወስድ አፈጻጸሙ በራሱ የሚናገርነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የአስተዳደሩ ምንጭ እንደሚሉት መንግሥት በአዲስ አበባበዓመት ለቤቶች ግንባታ ብቻ ከ2 እስከ 3 ቢሊየን ብር እያወጣ መሆኑን አስታውሰው ከዚህ በላይ ለማውጣት የፋይናንስ አቅም ችግር መኖሩን፣ገንዘቡ ቢገኝም በግንባታ አፈጻጸምበኩል የአቅም ችግር በመኖሩ በአጭር ጊዜ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ለመመለስ የማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንደገለጹት ደግሞ ዲያስፖራው በፈለገበት አካባቢ ቤት ለመስራት ይችል ዘንድ ክልሎች መመሪያ እንዲያወጡ መታዘዙን ገልጸዋል። ሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ የሆነ መመሪያ ባለማውጣታቸው ለዲያስፖራው ቤት ለማደል የታቀደው እቅድ የተፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ኢሳት የአዲስ አበባን አዲሱን ካርታ ዝግጅት አስመልክቶ ከወራት በፊት በሰራው ዘገባ፣ የቤት ግንባታ መርሃግብሩ የተሰናከለው በአዲስ አበባ የቤት መስሪያ ባዶ ቦታ በመጥፋቱ ነው። ቀደም ብሎ የኦሮምያን ልዩ ዞኖች ወደ አዲስ አበባ በመጠቅለል የቤት መስሪያ ቦታዎችን ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የኦሮምያ ክልል አንዳንድ ባለስልጣናትና አብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ በመቃወሙ እቅዱን በቀላሉ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። ዲያስፖራው ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ቦታዎችን እንዲጠይቅ ለማግባባት ኢምባሲዎች የስራ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ለአባይ ግድብ በቦንድ ስም ገንዘብ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ለማሰባሰብ የታቀደው እቅድ አለመሳካቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምነዋል። ከፍተኛ ገንዘብ ይገኝበታል የተባለው የአሜሪካ የቦንድ ሽያጭ አምና ጭራሽ አልተካሄደም ብሎ መናገር እንደሚቻል ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በሁሉም አገሮች ያለው የቦንድ ሽያጭ ደካማ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ፣ ለድክምቱ ዝርዝር ምክንያቶችን አላቀረቡም። የዶ/ር ቴዎድሮስ ገለጻ፣ ኢሳት ከዚህ ቀደም የቦንድ ሽያጩ በውጭ አገር አለመሳካቱን ሲዘግብ የቆየውን ያረጋገጠ ሆኗል። በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ገንዘብ ለመሰብሰብ በገዢው ፓርቲ በኩል የሚዘጋጁትን ዝግጅቶች አጥብቆ ሲቃወም እንደነበር ይታወቃል። አቶ መለስ የአባይን ግድብ እቅድ ይፋ ሲያደርጉ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ 1 ቢሊዮን ዶላር ያዋጣል የሚል እምነት ነበራቸው፣ ይሁን እንጅ እስካሁን ባለው መረጃ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊያዋጣ አልቻለም።

Sunday, 3 August 2014

በአንዋር መስጊድ ብጥብጥ ፖሊሶችም መሳተፋቸው ተገለጸ

-ኮማ ውስጥ ያሉ ተጎጂዎች ሁኔታ እስኪታወቅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በመርካቶ አንዋር መስጊድና በአካባቢው ላይ በተፈጠረ ግጭትና ብጥብጥ፣ አራት የፖሊስ አባላት መሳተፋቸው በፍርድ ቤት ተገለጸ፡፡ ፖሊስ ለሦስተኛ ጊዜ ሐምሌ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዮች ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ማስቻያ ችሎት 14 ተጠርጣሪዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን እያጣራ መልቀቁን ገልጾ በችሎቱ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ ለሚቀረው ተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የፈለገበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው አንድ ኢንስፔክተር፣ አንድ ምክትል ኢንስፔክተር፣ አንድ ምክትል ሳጂንና አንድ ኮንስታብል ግጭትና ብጥብጥ ከፈጠሩት ጋር በመተባበር ፀጥታ ለማስከበር በወጡ የሥራ ባልደረቦቻቸውና ሌሎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጎጂዎቹ በጥቁር አንበሳና በፖሊስ ሆስፒታል ኮማ ውስጥ ስለሆኑ በመሆናቸው ቃል አለመቀበሉን ገልጿል፡፡ ተጎጂዎቹን አሁን ባሉበት ሁኔታ ማናገርና ቃል መቀበል ባለመቻሉ፣ በቀጣይ የሚሻላቸው ከሆነ የእነሱን ቃል ለመቀበልና ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል የመቀበል ሥራ እንደሚቀረው ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ ሌሎች በግጭቱና ብጥብጡ የተሳተፉና የሚይዛቸው ተጠርጣሪዎች እንዳሉት ፖሊስ አስረድቶ፣ በሆስፒታል ውስጥ በሞትና በሕይወት መካከል ያሉት ተጎጂዎች ሁኔታ ሳይለይለት ለተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ሊፈቀድ እንደማይገባ አመልክቷል፡፡ የተጎዱት ሰዎች ቢሞቱ ተጠርጣሪዎቹ የሚቀርብባቸው ክስ የመግደል ወንጀል ክስ ሊሆን ስለሚችል፣ በወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 63 መሠረት ዋስትና ሊከለከሉ እንደሚችሉ መርማሪ ፖሊስ በመጠቆም የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡ በግጭቱ ወቅት አንድ ተጠርጣሪ ሆዱ አካባቢ በጥይት ተመትቶ የነበረ ሲሆን፣ ቀዶ ሕክምና የተደረገለት ቢሆንም ጥይቱ ከሆዱ ሊወጣ ባይችልም፣ በወቅቱ በግጭቱ በነበረው ተሳትፎ ምክንያት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ግለሰቡ በጥይት እንዴት ሊመታ እንደቻለና ማን እንደመታው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለፍርድ ቤት ተናግሯል፡፡ የአዲስ ጉዳይ ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድና የሰማያዊ ፓርቲ አባል ወ/ት ወይንሸት ሞላ፣ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ከተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል ናቸው፡፡ ፖሊስ ስለነሱ የወንጀል ተሳትፎ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፣ በግጭቱ ወቅት ሕዝቡ ሲሸሽ ‹‹ወንድ ሆነህ የት ነው የምትሸሸው?›› በማለትና ወደ ግጭቱ እንዲመለሱ በማድረግ፣ ግጭቱን ሲያባብሱ እንደነበር የሚያሳይ በቪዲዮ የተደገፈ ማስረጃ እንዳለው በማስረዳት ዋስትናቸውን ተቃውሟል፡፡ እነሱ አደፋፍረው ባባባሱት ግጭት የተጎዱና በሆስፒታል ኮማ ውስጥ ያሉ ተጎጂዎች ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ዋስትና እንዳይፈቀድላቸው ፖሊስ አመልክቷል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ፖሊስ ሆስፒታል፣ ተጎጂዎቹ ያሉበትን ደረጃ የሚገልጽ ማስረጃ እንዲልኩ በችሎት በመንገርና ፖሊስ ቀረኝ የሚለውን ምርመራ በአጭር ቀናት እንዲያጠናቅቅ በማዘዝ ለሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡