Thursday, 26 June 2014
በዓለም አቀፉ የሠላም ደረጃ ኢትዮጵያ ከ162 ሀገራት 139ኛ ደረጃን ያዘች
በየዓመቱ የየሀገራትን የሠላም ይዞታ በማጥናት ደረጃን የሚያወጣው ኢኒስቲትዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም የ2014 የዓለም ሀገራት የሰላም ደረጃ ከሰሞኑ የለቀቀ ሲሆን በዚህም ጥናቱ ከ162 ሀገራት ኢትዮጵያን በ139ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል። ተቋሙ የአንድን ሀገር የሠላም ደረጃ ለማውጣት በርካታ የስኬት ማሳያዎች (Indicators) ግምት ውስጥ ያስገባል። ለዚሁ ልኬት ግብዓትነት ከሚውሉት መመዘኛዎች መካከል የውስጥና የውጭ ግጭቶች፣ አንድ ሀገር ከጎሬበቶቹ ጋር ያለው የግንኙነት ሁኔታ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሽብር ተጋላጭነት፣ የወንጀል መስፋፋት እንዲሁም በእያንዳንድ አንድ መቶ ሺ ሰው በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን የእስረኛ ብዛትንም በመውሰድ ደረጃውን ለማውጣት በልኬትነት ይጠቀማል። ከዚህም በተጨማሪ ከአጠቃላይ ብሄራዊው ምርት አንፃር ለሚሊተሪው ዘርፍ የሚወጣውንም የገንዘብ መጠን ታሳቢ ያደርጋል። እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ ግብዓቶችን በማካተት ነው መረጃዎቹ ተተንትነው ደረጃ ወደ ማውጣቱ ስራ የሚካሄደው።
የየሀገራቱ ደረጃ ወጥቶ በድርጅቱ ድረገፅ እንዲሁም በዘ ኢኮኖሚስት መፅሄት ለህትመት የሚበቃ ሲሆን የዘንድሮውም ሪፖርት የ162 ሀገራትን መረጃ በመውሰድ ሰፊ ትንታኔ ከሰጠ በኋላ ኢትዮጵያ በ139ኛ ደረጃ አስቀምጧል። ተቋሙ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበት ሁኔታ በመግለፅም በይደር የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑንም አመልክቷል። ኢትዮጵያ ከፀጥታ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ገንዘብ የምታወጣ መሆኑን መረጃው ጨምሮ አመልክቷል። በዚህ የሀገራት የሰላም ደረጃ አይስላንድ የመጀመሪያውን ደረጃ በመያዝ በዓለም እጅግ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ተብላለች። ዴንማርክ ሁለተኛ ስትሆን ኦስትሪያ የሶስተኝነትን ደረጃን ይዛለች።
ከ162ቱ ሀገራት 162ኛን ደረጃ በመያዝ በደረጃው ግርጌ ላይ የተቀመጠችው ሶርያ ናት። አፍጋስታን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኢራቅ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም በደረጃው የመጨረሻ ግርጌ ላይ የተቀመጡ ሀገራት ናቸው። ግብፅ 148ኛ ደረጃን ይዛለች።
ዓለም አቀፍ የሀገራት የሠላም ስኬት ደረጃ (Global peace Index) በኢንስቲትዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ ተቋም በየዓመቱ ይፋ የሚሆን ሲሆን መረጃውን በማሰባሰቡ በኩል በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰፊ ትብብርና ተሳትፎን ያደርጋሉ። ከዓለም አቀፍ ተቋማቱ መካከል የተለያዩ የተባበሩት መንግስታት አካላትም ይገኙበታል። እንደ ኮፊ አናን እና ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱን የመሳሰሉና በተለያዩ ጊዜያት ሀገራትን ከመሩ በኋላ የስልጣን ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሪዎችም የሙያ አስተዋፅዖችን የሚያበረክቱበት ተቋም ነው። ተቋሙ የሀገራትን የሠላም ደረጃ የሚያወጣው 22 መስፈርቶችን አስቀምጦ በዚያ ልኬት መሰረት ነው።
Friday, 20 June 2014
ቀና ብለን የምንሄድበት ጊዜ አየመጣ ነው! ጎበዝ ተነሳ!
ጉጅሌዎቹ አይገባቸውም እንጂ የኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች የለውጥን ደመና ኣርግዘዋል። ወንዞችም ተራሮችም የለውጥ ማዕበል ማቆብቆቡን አያበሰሩ ናቸው። የቀደሙት ገዢዎች መረጃ የሚያገኙት እረኛ ምን ይላል ብለዉ እየጠየቁ ነበር። የአሁኖቹ አገር አጥፊ ገዢዎች ምሳሌ ያደረጉት ካድሬዎቻቸውን ብቻ ሆነ እንጂ ዛሬም የአገራችን እረኞች የለውጥን መምጣት በሚያምር ቅላጽያቸው አያንጎራጎሩ እንዲህ አያሉን ነው፣
የሀገሬ ጉብል የሰማውን እንጃ
የጎንደሬው ጉብል የሰማውን እንጃ
ከብቱን አየሸጠ ገዛ ኣሉ ጠብመንጃ።
የወለጋው ጉብል የሰማውን እንጃ
ቡናውን ሻሽጦ ገዛ ኣሉ ጠብመንጃ።
መልእክቱ ግልጽ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች አገራቸውን በክቡር ደማቸው ሊታደጓት ቆርጠው በመነሳት ወያኔን በማስወገድ የሀገራቸው ባለቤት ለመሆንና ያልተከፋፈለች ውብ ኢትዮጵያን ማየትን ለማረጋገጥ ጥርጊያውን መጀመራቸው ነው።
ላለፉት ፵ አመታት አምባገነኖች ባደረሱብን ጭቆና እና እንግልት የተነሳ የራሳችን የሆነ መንግሥት ሳይኖረን አንገታችንን ደፍተን ጀግኖቻችንን ስንገብር ኖረናል። በተለይም ባለፉት ፪፫ አመታት ጉጅሌዎቹ በአራት ኪሎ ከነገብን ጀምሮ በአንድ ላይ አንዳንቆም በማድረግና እና አርስ በራሳችን በማጋጨት ሲያባሉን ኖረዋል።
ዛሬ ሁኔታዎች ተለውጠዋል፤ በውጭም በአገር ውስጥም ለውጥ አየታየ ነው። የእንቅስቃሴው ማእበል አይሎ እየመጣ ነው። ዛሬ ሁሉም የዴሞክራሲ ሀይሎች ማለት በሚቻል ደረጃ በሁለት ነገሮች ላይ ስምምነት አለ፣
፩. ተቃዋሚዎች በግል ከሚያደርጉት ትግል ይልቅ በጋራ የመሰባሰብን አስፈላጊነት ተረድትው መሰባሰብ መጀመራቸው
፪. በአንድ ላይ መሰባሰብ ካልቻሉም እርስ በራስ ላለመጠላለፍ መስማማት መቻላቸውና አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ግዜ ሁሉ መረዳዳት መጀመራቸውና በግልም ከወያኔ ጋር የሚደረገውን ትግል ማፋፋም የቻሉበት ሁኔታ አየታየ መሆኑ የሕዝብ ወገኖችን እያስደሰተ ይገኛል።
በአገር ቤት የሚገኙ የዴሞክራሲ ኃይሎችም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕዝቡ ከፍርሀት ተላቆ ለመብቱ አንዲነሳ የሚያደርጓቸው አንቅስቃሴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ መጥተዋል። ለዚህም በቅርቡ በአዲስ ኣበባ መድረክ፣ ኣንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች የጠሯቸው ሰልፎች ይበል የሚያስብሉ ናቸው።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ በዚሀ ኣጋጣሚ ለዴሞክራሲና ለነፃነት ታጋዮች ሁሉ ያለውን አክብሮትና ኣድናቆት ይገልጻል።
በሌላም በተለያዩ አቅጣጫዎች ወያኔን በኣመጽ ለመፋለም የወሰኑ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ወያኔን ለመፋለም ቆርጠው በጋራ ክንዳቸውን ኣቀናጅተው ለመፋለም አየተዘጋጁ ያሉበት ሁኔታ አበራታች ነው። እነዚህ ኃይሎች አዳዲስ የነጻነት ታጋይ አርበኞችን በተከታታይ በማስመረቅ ያሉ መሆናቸውና ከዚህም በተጨማሪ ከመላው የአገሪቱ አካባቢዎች ወጣቶች በገፍ ትግሉን እየተቀላቀሉ መሆኑን ስንሰማ ልባችን በደስታ ይሞላል።
በወያኔ ጉያ ውስጥ ያሉ የሕዝብ ወገኖች ደግሞ የቻሉትን በውስጥ ሆነው መቃብሩን እይቆፈሩለት ሲሆን፣ ያልቻሉትም የወያኔን ሚስጢር ይዘው በመውጣት የሕዝብ ወገንተኝነታቸውን አየገለጹ ይገኛሉ።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ለመላው ሕዝባችንና በተለይም ለወጣቱ ትውልድ በተደጋጋሚ አንደሚለው የሀገራችን ባለቤት ለመሆን የምናደርገውን ትግል ተቀላቀሉ!!! መቀላቀል ያልቻላችሁም በኣካባቢያችሁ ከምታምኗቸው ወገኖቻችሁ ጋር ተሰባሰቡ፣ በህዋስ ተደራጁ። ግንቦት 7 በዚህ ትግል የዳር ተመልካች ሳይሆን መሪ እንድትሆኑ ኣገራዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
Saturday, 14 June 2014
በአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደር ቢሮና በሌሎች ተቋማት ላይ ፓርላማ ዕርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ
ዋና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂዋ ወ/ሮ ፎዚያ አሜን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲያቀርቡ፣ ተቋሙ በምርምራ ውጤት ላይ ተመሥርቶ የተሠሩ ጥፋቶች እንዲታረሙና በደል የደረሰባቸው መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሥራ ኃላፊዎች ከክልሎች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር፣ አብዛኞቹ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሚቀርቡባቸውን አቤቱታዎች እንዲያርሙና የተበደሉ ደግሞ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን በበጐ ጐኑ አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በምርምራ ላይ ተመሥርቶ የሚያቀርብላቸውን የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊ ካለማድረጋቸውም በላይ፣ የማይተገብሩበትን ምክንያት እንኳን አይገልጹም ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የሕግና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በልዩ ሁኔታ እንዲከታተላቸው ዝርዝር ሪፖርት እንደተላከለትና ኮሚቴውም በአሁኑ ወቅት አስፈላጊውን ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዝርዝር ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ከተላለፉ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ይገኙበታል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ የተጠቀሱት ተቋማት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የእንስሳት ሰብልና ገጠር ልማት ቢሮ፣ የሐረር ክልል ፍትሕና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ ናቸው፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአሥር ወራት ጊዜ ውስጥ 2,948 የአቤቱታ መዝገቦች የቀረቡለት መሆኑን የገለጹት ዋና እንባ ጠባቂ ወ/ሮ ፎዚያ፣ መዝገቦቹ በአጠቃላይ 17,682 አቤቱታ አቅራቢዎችን ይመለከታሉ ብለዋል፡፡
Tuesday, 10 June 2014
“ስለ ….. ሲባል ምርጫ ይቅር” …. ትግሉም ይቁም ወይ? ግርማ ሠይፉ ማሩ
“ስለ …. ሲባል ምርጫ ይቅር” በሚል እንድ ፅሁፍ ፋክት ላይ ወጥቶ አንብቤ ለምን? ብዬ ልፅፍ አስቤ ተውኩት፡
፡ ምክንያቱም በፋክት መፅሔት ላይ አምደኞች የሃሣብ ፍጭት ማድረግ የተለመደ ቢሆንም ሰሞኑን ግን የበዛ
ይመስላል ከሚል ነበር፡፡ ይህ አንድ ዘርፈ ብሉ ጥሩ ጎን አለው፡፡ አንዱ አምደኞቹ ከአንድ ፋብሪካ የወጡ ሳሙና
ዓይነት ያለመሆናቸውን ያሳያል፡፡ሌላው የፋክት መንፈስ ብለው ለሚቃዡትም ሆነ፤ ከመሬት ተነስተው
ለሚፈርጁት የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡ ጉዳቱ ደግሞ በሳምንት አንዴ ብቅ ለምትል መፅሄት የተወሰነ
ሃሳብ በተወሰኑ ሰዎች የሚቧቀሱባት ከሆነች ደግሞ አንባቢን አማራጭ እንዳያሳጣ የሚል ፍርሃት ስለአለኝ፡፡ ይህ
ሁሉ ዳር ዳርታ እኔም ተውኩት ወዳልኩት የሃሣብ ፍጭት ለመቀላቀል ሰበብ ፈልጌ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርቡ
“ሰለ … ሲባል ምርጫ ይቅርብን” በሚል በወዳጄ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ያቀረበውን ሃሳብ ባልቀበለውም
በፋክት ላይ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እናደርጋለን ብዬ እያሰብኩ ሳለ በፌስ ቡክ የውስጥ መዘገቢያ
እንዲሁም በግል የሚያገኙን ሰዎች ምርጫ እንዳትወዳደሩ የሚል አንዳንዱ ምክር አንድ አንዱ ደግሞ ትዕዛዝ
መሰል መልዕክቶች በብዛት ይደርሱኝ ጀምረዋል፡፡ ውሳኔው ልከም ይሁን አይሁን የምርጫ ጉዳይ የሚወሰነው
በፓርቲ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የግል አስተያየቴን መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ነው “ሰለ … ሲባል ምርጫ ይቅር” ከተባለ እኔም እንደቅድመ ሁኔታ ትግሉም ይቁም ወይ? በሚል ጥያቄ የጀመርኩት፡፡
በእኔ እምነት ምርጫ መወዳድር ያለመወዳደር የሚባል አማራጭ የለም፡፡ የአንድ ፓርቲ ስራ ምርጫ መወዳድር ነው፡፡ የሰው ልጅ ሞት እንዳለ እያወቀ ሞትን ረስቶ በህይወት እንደሚኖረው ማለት ነው፡፡ ለፓርቲዎች ያለመወዳደር የሚባል ነገር እንዳለ ረስተው ለምርጫ ውድድር መዘጋጀት ዋናው ስራቸው መሆን አለበት፡፡ ፓርቲዎች ምርጫ ላለመወዳደር የሚያበቃ ነገር እንዳይኖር ተግተው መስራትን ትተው፤ ላለመወዳድር ሰበብ የሚፈልጉ ከሆነ እንደ አሸዋ የበዛ ሰበብ ማቅረብ አይገድም፡፡ ከዚህ ሰበብ ውስጥ ግን አንድም ተሰፋ አይገኝም፡፡ ምርጫውም የሰነፍ ነው የሚሆነው እንጂ ባስቸገሪ ሁኔታ ጀግና ለመሆን ለሚታትር ታጋይ የሚመጥን አይደለም፡፡ በሀገራቸን ኢትዮጵያ ለምርጫ የእኩል መወዳደሪያ ሰፍራ ሳይኖር ምርጫ መወደዳር አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳት ለማንም የሚገድ አይደለም፡፡ ትግል የሚባለው ነገርም የመጣው ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ በመኖሩ ነው፡፡ በአሜሪካን ወይም በሌሎች በዲሞክራሲ በዳበሩ አገሮች የሚደረግ የፖለቲካ ተሳትፎ ትግል አይባልም፡፡ ታጋዮች ማድረግ ያለባቸው ታዲያ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማስወገድ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚያስፈልገውን ማድረግ ነው፡፡ ክቡር የሆነውን የስው ልጅ ህይወት ከማጥፋትና ንብረት ከማውደም በመለስ ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ ቢባል በምርጫ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ናቸው ብዬ የማምናቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በማንሳት ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
የዕጩ ተወዳዳሪ ዝግጅት አንዱ መስረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በምርጫ ለመወዳድር የወሰነ አንድ ፓርቲ በምንም ዓይነት መልኩ ርጫው
ሲደርስ ዕጩ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና የሚል ከሆነ ለመሸነፍ መዋጮ ማድረጉን ማመን አለበት፡፡ ለምርጫ ውድድር የሚመለመሉ ጩዎች በሁሉም መልክ በተለይ ከገዢው ፓርቲና መንግሰት ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና ለመቋቋም ዝግጁ የሆኑ መሆን አለባቸው፡፡ በዋነኝነት እነዚህ ዕጩዎች እንደ ገዢው ፓርቲ ወጪያቸው በፓርቲ የሚሸፈን ባለመሆኑ ተገቢውን ፋይናንስ ከደጋፊዎቻቸው ለማግኘት የሚያስችል ስልት መቀየስ የግድ ይላቸዋል፡፡ ውድድሩ በእኩል ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ከሚያስረዱት ሁኔታዎች አንዱ ይህ ነው፡፡ የገዢው ፓርቲ ዕጩዎች በዚህ ጉዳይ ቅንጣት ሃሣብ የለባቸውም፡፡ ይህ ጉዳይ የምርጫ ትግል ከሚደረግባቸው አንዱ መሆኑን ተረድተን መፍትሔ መሻት የእኛ እንጂ አንድ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉ ፓርቲዎች እንደሚሉት ለዚህ መፍትሔ ኢህአዴግ/መንግሰት የገንዘብ ድጋፍ ያድርግልን የሚለው አይደለም፡፡ በሀገራችን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና መንግሰት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ከሚባለው በላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ መንግሰት ድጋፍ ያድርግልን ሲባል ኢህአዴግ ያድርግ እንደማለት እየሆነ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ይህን አድርጎ ለመሸነፍ ዝግጁ አይደለም ሰለዚህ ታግለን ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በፍትሃዊነት የሚታዩበት ስርዓት እንዲመጣ በትግል ውስጥ ያለን መሆኑን መረዳት የግድ ይለናል፡፡ ይህ ከባድ ከሆነ አማራጩ ትግሉ ይቅር ወይ? የሚለው ነው፡፡
ከዕጩ ዝግጅት በኋላ በዋነኝነት የሚያስፈልገው በየደረጃው ያሉ ታዛቢዎችን ማዘጋጀት ነው፡፡ የታዛቢዎች ዝግጅት በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት የሚዘጋጁት ታዛቢዎች ማለትም “የህዝብ ታዛቢ” የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ታዛቢዎች በሚመረጡበት ጊዜ ኢህአዴግ ቀደም ብሎ በአንደ-ለአምስት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በወጣትና ሴቶች ፎረም ያደራጃቸውን በተለይም የፋይናንስ አቅማቸው ደከም ያሉ የአካባቢ ነዋሪዎችን በማዘጋጀት በህዝብ እንደተመረጡ በማስመሰል ይመድባቸዋል፡፡ ይህ ሲፈፀም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በዝምታ በማለፍ አንድ ደጋፊያቸው እንኳን እንዲገባ ሳያደርጉ ያልፋሉ፡፡ ትግሉን በትክክል ተረድተን ከሆነ በየምርጫ ጣቢያዎች እነዚህ ታዛቢዎች ሲመደቡ እኛም ደጋፊዎቻችን እንዲኖሩ ለማድረግ መስራት ይኖርብናል፡፡ ልክ ነው ይህን ለማድረግ ኢህአዴግ የዘረጋው ዓይነት የመንግሰት መረብና ድጋፍ አናገኝም፡፡ ይህ ነው የውድድር ሜዳው ልክ አይደለም የሚያስብለው እና ትግል የሚያስፈለገው፡፡ ይህን ለመለወጥ ትግል ማድረግ ካለብን የማይቻል አይደለም፡፡ ሁሉተኛው በዕጩ ተወዳዳሪዎች በራሳቸው የሚመደቡ ታዛቢዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ታዛቢዎች የመምረጥ መብት የዕጩ ተወዳዳሪው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ያለው ፈታኝ ነገር ታዛቢዎችን ማስፈራራት፣ በገንዘብ መደለል ሲበዛም አፍኖ መውሰድ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ በሙሉ የትግሉን አስፈላጊነት የሚያሳዩ እንጂ እንዲህ ግርማ ሠይፉ ማሩ ከሆነማ ምርጫ ይቅር የሚያስብሉ አይመስለኝም፡፡ የማይፈራ፣ በገንዘብ የማይደለል ታፍኖ ለሚደርስበት ፈተና የተዘጋጀ ታዛቢ ማዘጋጅት
ትግሉ የሚጠይቀው መሰዋዕትነት ነው፡፡ ለዚህ የሚመጥን ታዛቢ ማዘጋጀት የዕጩ ተወዳዳሪዎችና የፓርቲዎች ሲሆን ይህን በታዛቢዎች ላይ የሚፈፀም ህገወጥ ድርጊት ማሰቀየር ነው በሀገራችን ፖለቲካ ከሌሎች ዲሞክራሲ ከሰፈነባቸው ሀገሮች ለየት የሚያደርገው እና ትግል ያሰፈለገው፡፡ ምርጫቻን የቱ ነው? ታግለን እንቀይር ወይስ ኢህአዴግ በቃኝ እስኪል እንጠብቅ ነው፡፡
የመራጮች ምዝገባ ዘወትር ተገቢ ትኩረት የማይሰጠው በተወዳዳሪ ፓርቲዎች በኩል ነው፡፡ በ1997 ምርጫ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቅስቀሳ ተደርጎ ብዙ መራጭ የተመዘገበ ቢሆንም መምረጥ የሚገባቸው ያልተመዘገቡና ባለመመዝገባቸው የቆጫቻ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ የ1997 በተለየ ሁኔታ ትተን በሌሎች ምርጫዎች ተቃዋሚዎች እንዲመርጡን የምንፈልገው ኢህአዴግ ጎትጉቶ ባስመዘገባቸው መራጮች ነው፡፡ ሁሉም ማወቅ ያለበት ኢህአዴግ በመራጭነት እንዲመዘገቡ ቤት ለቤት እየሄደ የሚቀሰቅሰው ባለው መረጃ መሰረት ደጋፊዎች ብሎ ያመነባቸውን ወይም በቀላሉ ደጋፊ ላደርጋቸው እችላለሁ ብሎ የሚገምታቸውን ነው፡፡ በተለይ በትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እናቶች ከአባለት ቀጥለው ለምዝገባ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ፓርቲዎች በምርጫ ትርጉም ያለው ለውጥ ማየት የምንፈልግ ከሆነ የመራጭ ምዝገባ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ደጋፊዎች እንዲመዘገቡ መቀስቀስ፣ ማበረታት እንዲሁም የመመዝገብን ጥቅም ማስተማር ይኖርብናል፡፡ ፓርቲዎች ላለመወዳደር ቢወስኑ እንኳን ደጋፊዎቻቸው ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይሄዱ ማድረግ በምርጫው ላይ ትርጉም ያለው መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ያለመወዳደር ምርጫ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ መራጮችን ለማሰመዝገብ በምናደርገው እንቅስቃሴ በአብዛኛው ችግር ባይኖርም መዝጋቢ የለም፣ መታወቂያ አልታደሰም፣ እሰከ ዛሬ የት ነበርክ፣ በቀበሌ ተሳትፎ የለህም፣ የመሳሰሉት የሚጠበቁ የማደናቀፊያ መንገዶች ናቸው፡፡ ይህን ሊቋቋም የሚችል መራጭ እንዲኖር ቅስቀሳ ማድረግ ከትግሉ አንዱ አካል ነው፡፡ መራጮች በወኔ እንዲመዘገቡ ካደረግናቸው ከተመዘገቡ በኋላ መራጭ ብቻ ሳይሆን ቀስቃሽም በመሆን የምርጫ ምዕዳሩ እንዲስተካከል ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ህዝብ የተሳተፈበት አፈናን እንቢ የማለት ተግባር ደግሞ በጥቂት ካድሬዎች ቁጥጥር ስር እንዲውል የተውነውን ምርጫ በትግላችን የእኛም ይሆናል ማለት፡፡ ለመምረጥ ያልተመዘገበ መራጫ የምርጫ ምዕዳር ለማስፋት አላፊነት ያለበት አይመስለውም፡፡ ትክክልም ነው፡፡ የምርጫ ምዕዳር የማስፋት አላፊነት ያለበት ዜጋ መፍጠር የትግሉ አካል ነው፡፡ ቆጠራ ሳይጠናቀቅ ካደረ አብረን ስንጠብቅ እናድራለን የሚል መራጭ ማዘጋጀት የግድ ይላል፡፡ ምርጫ 97 ትዝ አይላችሁም፡፡
መራጮች የሰጡትን ድምፅ፣ ታዛቢ ተከታትሎ ቆጥሮ፣ ደምሮ የተቀበለውን፣ ምርጫ ቦርድ ሊለውጠው አይችልም ባይባልም ለመለወጥ የሚገጥመው ፈተና ከባድ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ እንደመፃፍ ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል፣ ኢህአዴግ ሲጨንቀው በታጣቂ ኮሮጆ እንደሚገለብጥ ዘንግቼው አይደለም፡፡ ይህን ድርጊቱን በተደራጀ መከላከል የትግሉ አንድ አካል እንደሆነ አፅዕኖት ለመስጠት ነው፡፡ ፓርቲዎች አሁን ባለው ደረጃ ይህን ለማድረግ ሙሉ ለሙሉ አልተዘጋጀንም የሚሉ ከሆነ ከምርጫ ለመውጣት ሳይሆን በተደራጁበት ልክ ለመወዳደር መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሀሉም ቦታ ለመሆን ሲከጀል አንድም ቦታ ያለመሆን የሚመጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በታዛቢዎች የተፈረመ የምርጫ ውጤትን በምርጫ ቦርድ በኩል በሚፈፀም ሸፍጥ ወይም በጉልበት መሣሪያ ጭምር ተደርጎ በሚደረግ ንጥቂያ ሌላ ፈተና ላይ የሚወድቀው አካል የፍትህ ስርዓቱ ነው፡፡ የተደራጀ መረጃ ይዘን የፍትህ ስርዓቱን መሞገትም አንዱ የትግል አካል እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህን ሁሉ አድርገን ኢህአዴግ እነዚህን የህዝብ ድምፆች ገፍቶ ማነኛውንም ዓይነት ጉልበት ለመጠቀም ቢወስን ህዝብ የተሳተፈበት ስለሚሆን መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ምርጫን ተከትሎ ለሚመጣ አብዮትም ጠሪ የሚሆነው የዚህ ዓይነት ድርጊት ነው፡፡ በምርጫ መሳተፍ ሂደት ውስጥ ህዝብ ካልተሳተፈ የተወሰኑ ሰዎች የሚያደርጉት መፍጨርጨር ሰለሚሆኑ ህዝቡ ድምፁ እንዲከበር የሚያደርገው ግፊት እምብዛም ነው፡፡ እነደከዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ወትውቶ ያስመዘገባቸው ሰዎች ለምን አልመረጡንም ብለን መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ በሚስጥር ድምፅ ሰጥተውን ቢሆን እንኳ በይፋ ድምፃችን ይከበር ሊሉ ይችላሉ ብሎ መጠበቅ የዋህ መሆን ነው፡፡ በሚስጥር የካዱትን በአደባባይ እንዲያረጋግጡ መጠየቅ ነው የሚሆነው፡፡
በዚህ ደረጃ ሳንዘጋጅ ቀርተን ምዕዳሩ ጠቧል ብለን “ሰለ …ሲባል ምርጫው ቢቀር” የምንል ከሆነ ኢህአዴግ ደስተኛ ነው፡፡ በግልፅ የሚሰብከውን አውራ ፓርቲ ስርዓት ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ኢህአዴግ ምዕዳሩን በህዝብ ተሳትፎ ሳናስገድደው ያሰፋዋል ብለን የምንጠብቅ ከሆነ በቅርቡ የሚሆን ስለአልሆነ የትግል ስልታችንን መፈተሸ ሊኖርብን ይገባል፡፡ አንዱ አማራጭ አንድ ሺ ትንታግ ታዛቢ ከማዘጋጀት፣ አንድ ሺ ተኳሽ ተዋጊ ሀይል ማዘጋጅት ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ ዘመኑ የሚዋጀውን፣ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን፣ በወጪ አንፃርም አዋጭ ሊሆን የሚችለውን የትግል ስልት መምረጥ በፓርቲ ውስጥ ያሉ ስትራቴጂሰቶች ሃላፊነት ነው፡፡ በሃላፊነት ሰሜት የሚወሰን፡፡
እርግጠኛ ነኝ “ስለ …. ሲባል ምርጫው ቢቀር” የሚለው ሃሳብ የቀረበው በባርነት እንቀጥል በሚል ወይም የኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ፍልስፍና ተስማምቶናል የሚል አይደለም፡፡ በእኔ አረዳድ ሌላ አማራጭ የትግል ስልት እንመልከት የሚል መሆን አለበት፡፡ ለጊዜው የምርጫው መንገድ ገና ብዙ ያልተሄደበት መንገድ ስለሆነ ተሰፋ መቁረጥ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ምርጫ መሳተፍ የሰላማዊ ትግል ማሳኪያ አንዱ መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን በፍፁም የምርጫ ሰሞን ደርሶ በሚፈጠር ሆይ ሆይታ ውስጥ ውጤት ለማግኘት መከጀል አይደለም፡፡ ከላይ በአጭሩ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት በሁሉም የምርጫ ደረጃዎች በንቃት በመሳተፍ እና ህዝቡን በማሳተፍ ነው፡፡
ቸር ይግጠመን
Friday, 6 June 2014
የደህንነት ኃይሎች በጋዜጣ አዙዋሪዎች ላይ እርምጃ መወሰድ ጀመሩ
(ነገረ-ኢትዮጵያ፣ ሰበር ዜና) – በቅርቡ ገዥው ፓርቲ የግሉን ሚዲያ ለማፈን እንዲያስችል ጋዜጣ አዙዋሪዎችና አከፋፋዮችን በጥቃቅንና አነስተኛ ለማደራጀት የሚያስችል አሰራር እንደጀመረ ታውቋል፡፡ በዚህ አሰራር መሰረት ገዥው ፓርቲን የሚተቹ ጋዜጦችና መጽሄቶች ከገበያ በማስወጣት በቀጣዩ ምርጫ የሚደርስበትን ጫና ለመቀነስ እንደፈለገም ሲነገር ቆይቷል፡፡
ይህ በአዙዋሪዎች ላይ ሊወሰድ የታቀደው እርምጃ ዛሬ አመሻሹ ላይ የጀመረ ሲሆን በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ጋዜጣ አዙዋሪዎች በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች ታግተው አምሽተዋል፡፡ በእገታው ወቅት የደህንነት ኃይሎች ‹‹ለማዞር የተደራጃችሁበትንና ፈቃድ የተሰጣችሁበትን ወረቀት አምጡ›› በማለት ወደ ጣቢያ ሊወስዱዋቸው እንደነበርና አዙዋሪዎቹም ‹‹መደራጀት አይጠበቅብንም፣ ጣቢያም አንሄድም›› ብለው የደህንነቶቹን ትዕዛዝ መቃወማቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም መንግስት የሚተቹትን ጋዜጦችና መጽሄቶች እንዲያዞሩ እንደማይፈልግና እሱ በሚፈልገው እያደራጀ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ እርምጃው መጠነ ሰፊ መሆኑን የጠቆሙት ታጋቾቹ ‹‹መንግስት ይህንን ለመተግበርም በእኛ ብቻ ሳይሆን ጋዜጣ በምናስነብብባቸው ካፌዎች ላይም ጫና ተጀምሯል፡፡ ካፌዎቹ ለአንድ ሰው ከአንድ ጋዜጣ በላይ እንዳንሰጥና አንዳንዶቹም ጭራሹን እንዳናስነብብና እንዳንሸጥ እየከለከሉን ነው፡፡›› ያሉት አዙዋሪዎቹ እስካሁን ይወሰዳል የተባለው እርምጃ ዛሬ በግልጽ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
Sunday, 1 June 2014
የሶስቱ የዞን 9 ጦማርያን "የፍርድ ቤት" ቆይታ
ለዛሬ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተጠይቆባቸው የነበረው ሶስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ማህሌት ፋንታሁን በፍቃዱ ሃይሉ እና አቤል ዋበላ ላይ ተጨማሪ 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡ ፓሊስ የጠየቀው 28 ቀን የተፈቀደለት ሲሆን ማንም የቤተሰብ አባል ችሎቱ ውስጥ ያልተገኘበት ዝግ ችሎት ነበር፡፡
ጦማርያኖቹ ለደቂቃዎች ችሎቱ ውስጥ ቆይተው ከመውጣታቸው በፌት ጊቢ ውስጥ ያሉ ቤተሰብ ጓደኞች ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ሊከታተሉ የመጡ ሰዎችን ከግቢው አንዲወጡ ፓሊስ አስገድዷል፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ "ፍርድ ቤት" ጊቢው ሲገቡ አንጂ ሲወጡ ቤተሰብና ወዳጅ ሊያያቸው አልቻለም፡፡ በዛሬው ችሎትቤተሰብ አባላት ላይ ከፍተኛ ወከባና እንግልት የደረሰ ሲሆን ብዙ የቤተሰብ አባላትና የቅርብ ጓደኞች ሲያለቅሱ ታይተዋል፡፡
ማህሌት አቤልና በፍቃዱ በጠንካራ መንፈስ ላይ ሆነው የታዩ ሲሆን 28 ቀን መፈቀዱም ክሳቸው በጸረ ሽብር ህጉ እንደሚታይ ያመለክታል፡፡
የዞን9 ጦማሪያን ጓደኞቻችን ምንም አይነት የወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደማያቁ እና ክሳቸው ፓለቲካዊ እንደሆነ እያስታወስን በፍርድ ቤት ተገኝተው አጋርነታቸው ላሳዩ ከ120 በላይ ለሆኑ የዞን ዘጠኝ ወዳጆች ልባዊ ምስጋናችንን በታሰሩ ጓደኞቻችን ስም እናቀርባለን!
Subscribe to:
Posts (Atom)