Monday, 26 May 2014
አቶ ስብሃት ነጋ – የእንደራደር ጥያቄዎን በታማኒ ተግባር ይጀምሩት!
ከዚህ በፊት የግንቦት ሰባት ድርጅት የንደራደር ጥያቄ ከኢትዮጵይ መንግሥት አንደደረሰው በአፅኖት አውርቶናል። ብዙ ሕዝብ የግንቦት ሰባትን ዜና በማድቤት የተፈበረከ እራስን የመካቢያ ወሬ አድርጎት አንደነበር አይዘነጋም። እኔ ግን ዜናውን አንደወረድ መቀበል ብቻ ሳይሆን ደስተኛም ነበርሁ። ኢትዮጵያን አግዚአብሔር አንደሚጠብቃትም ያመንሁበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል። የዋህ ላገር ቅን አሳቢ ስለሆንህ እንጅ ከእባብ የርግብ አንቁላል እንዴት ትጠብቃለህ ብባልም የባብ መርዝም መዳህኒት ሊሆን እንደሚችል ይታወቅ ብያለሁ።TPLF power broker, Sibehat Nega
ከሁልም ያስደስተኝ ግን ግንቦት ሰባት ጥያቄውን በሕዝባዊ መግለጫው ያስተናገደበት ዘዴ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ድርጅቱ በኢሃዴግ ተጠይቆ ከሆነ ጉዳዩን በምስጢር ይዞ ማካሄድ ነበረበት ብለዋል። የሕዝብን ጉዳይ ይፋ ማድረጉ የሚአስመሰግነው እንጅ ሊአስወቅሰው አይገባም። ከሁሉም በጣም የሚአስደስተው ደግሞ ድርጅቱ ከመንግሥት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ ለድርድሩ ታማኒነት መንግሥት በቅድሚያ ማድረግ ያለበትን ነገሮች ይፋ ማድረጉ ነበር። በመሰረቱ ይህ ከፍተኛ የሆነ ያገር ጉዳይ ለህዝብ ምስጥር የሚሆንበት ምክንያት ውሃ የሚቋጥር አይሆንም። ድርድሩ ቢጀመር ግን ሂደቱን የሚአደናቅፉ ሁኔታውች አንዳይከሰቱ ሲባል በምስጢር ሊያዙ የሚችሉ ጉዳዮች ግን ይኖራሉ። በዚህ ድርጊቱ ግንቦት ሰባት የመንግሥትን ሀቀኝነት ፈትሾታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ስለሆነም የግንቦት ሰባት መግላጫ ቀለም ሳይደርቅ የመንግሥት መገናኛ ምኒስተር የማስተባበያ መግለጫ ወዲአው አወጣ። ማስተባበያውም በይዘቱ ቀላልና ተራ ሲሆን ድርጅቱን ኮንኖ ከመንግሥት ለተቃዋሚዎች ያቀረበው የንደራደር ጥያቄ አለመኖሩን አበሰረ። ልክ ተራ ሰዎች እንዳሉት መንግሥትም ግንቦት ሰባት እራሱን ለመኮፈስ የተጠቀመበት ባዶ ፕሮፖጋንዳ ነው አለ። መንግሥት የፖለቲካ ክስረትና ታማኒነት የጎደልው መሆኑን በራሱ አወጀ። መግለጫው መሰረተቢስ ቢሆን አንኳን መንግሥት ራሱን ከፍ አድርጎ በማየት የእንደራደር ጥያቄውን በኩራት ሊቀበለው በተገባ ነበር። በዚህም መንግሥት ከአጥቂነት ወደተከላካይነት ራሱን ዝቅ አድርጎ ታይቱዋል።
ያለእሳት ጭስ አይኖርም እንዲሉ ሰሞኑን በጀርመን የአማርኛ ራዲዎ ላይ በተደረገ ውይይት አቶ ስብሃት የንደራደር ጥያቄን በማያሻማ ሁኔታ ተናግረዋል። ኢትዮጵያን የገጠማት ዘርፈ ብዙ ችግር ለመፍታት ሕውሓትና ኢሓዴግ ከተቃዋሚወችና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋረ ለድርድርና ለውይይት ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት ባጽንኦት ገልጸዋል። እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል አንዲሉ በተቃዋሚ ጎራ የሚገኙ ሰዋች የአቶ ስብሃትን ጥሪ በከፍተኛ የጥርጣሬ ዓይን ተመልክተውታል። በተልይም የሕውሓትን የጀርባ አጥንት ከምስረታ ጀምሮ ስልጣን አስከያዘበት ገዜ ያለውን በሓሪ ለሚአውቁ ሁሉ ማመን ተስንዋቸዋል። ሆኖም ሌባ ይመጣል ተብሎ ሳይተኛ አይታደርም እንዲሉ የድርጅቱ ችግር አንዳለ ቢሆንም በወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች አስጋዳጅነት ይህ አይሆንም ማለት አይቻልም። እንደዚህ ጸሓፊ ግንዛቤ የፖለቲካ አስተያየት በወቅቱ ባለው የማህበራዊ፣ ኢኮነሚያዊ፣ ፖለቲካያዊ ጭብጥ ሀኔታና ገምግሞ መሰረታዊ አቋምን ማንጸባረቅ ግድ ይላል። በዚህ ላይ ስምምነት ከተገኘ ፖለቲካ ደግሞ መቻል በሚቻልበት ጊዜ የሚከናወን የኪነጥበብ ስራ (Politics is the Art of the Possible) ይሆናል ማለት ነው።
ወያኔ ኢሃዴግ ኢትዮጵያ አሁን ከፍተኛ አጣብቂኝና ብሎም መስቀለኛ መንገድ ላይ አንዳለች ተረድተዋል። ሁኔታው ባለበት ከቀጠለ አገር የሚባለው ነገርም ላይኖር ወደሚቻልበት አዝማሚያ አየተጓዘ መሆኑን ይገነዘባሉ። ሃያ ሶስት ዓመት ሙሉ በሕጋዊም ሆነ በሕገወት መንገድ የተካበተው ሃብት፤ ንብረትና እንገነባለን የተባለው የትግራይ ሪፑብሊክም እውን ወደማይሆንበት ደረጃ እደተደረሰና የሁሉም መጥፊያ መቃረቡን ከነሱ የበለጠ የሚረዳ አይኖርም። አርባ ዓመት ሙሉ ፖለቲካ ጸንሰው፤ ወልደው፤ አሳድገውና ተግብረው ፤ አኝከውና ተመግበው ያደጉ የህውሃት ሰዎች ይህን መጻኢ ችግር አይርዱም ብሎ የሚአስብ ተቃዋሚ ካለ የፖለቲካ ድርቅ የመታው በቻ ነው።
ሁላችንም ከምንጠፋ ተወያይተን ችግራችንን አንፍታ ብለው ቢአስቡ የሚደንቅ ካለመሆኑም በላይ ባብዛኛው ተጠቃሚ የሚሆኑት በስልጣን ላይ ያሉት ፖለቲከኞች ናቸው። ምክንያቱም በስልጣን፤ በሃብት፤ በምቾትና በብልጽግና የካበቱት እነርሱ ብቻ ስለሆኑ በሕይወትም ኪሳራ የሚደርሰው በመጀመሪያ በነሱ ላይ አንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ተቃዋሚውማ አሁን ካጣው በበለጠ ሊአጣው የሚችል የሃብት፤ የሕይወት፤ የንብረትና የኖሮ ኪሳራ ይኖራል የሚል እምነት አይኖርም። ተቃዋሚው ማጣት የማይፈልገው ነገር ቢኖር ሉአላዊነትዋ የተጠበቀች አንዲት አገርን ነው ። ይህ ደግሞ የሁላችንም ክስረትና መጥፊያ ስለሆነ ሁላችንም የድርሻችንን ማድረግ የተጠበቅብናል።
ስለዚህ አቶ ስብሃት ደጉን ነገር አስበዋልና እንቀበላቸው ። ለዚህ ምክንያቱ ብዙም ቢሆን ግለሰቡ የሕውሓት መስራች፤ የድርጅቱ አንጋፋ መሪ፤ የሕውሓት ዋና አማካሪና ተድማጭ በሎም ፈላጭ ቆራጭ በመሆናቸው ድርጅታቸውን በቀላሉ ያሳምናሎ በሎ መገመት ይቻላል። በተጫማሪ ትግራይና ሕዝብዋ በሕውሃት ላይ ፊቱን ካዞረ ቆይትዋል። መሰረታዊ የፖለቲካ አምባቸውን ማጣታቸውብዙ ተወርቶለታል። ለአረና ትግራይ ንቅናቄና አስተምህሮት ምስጋና ይግባውና።
እንደአብነት ለመጥቀስ ያህል ባለፉት ወራት የትግራይን ሕዝብ ድጋፍ ለመጠየቅና ለመቀሰቀስ አንጋፋዎቹ የሕውሃት መስራቾች ስብሃት ነጋ፤ አባይ ጽሐየ፤ ስዩም መስፍንና ዓባይ ወልዱ በተለያዩ አውራጃወችና ወረዳዎች ተዘዋውረው ሕዝቡን ለመቀስቀስ ሞከረዋል። በሁሉም ቦታ በሚባል ደረጃ የገጠማቸው ተቃውሞና ጥያቄ አንድወጥ ነበር። ከሕዝቡ የተሰጣቸው መለእክት መልክተኞችንና ድርጅታቸውን ከማሰደንገጡም ባሻገር አከርካሪአቸው ተሰብሮ በመጡበት አንዲመለሱ አንዳደረጋቸው በቅርብ የሚከታተለው አብርሃ በላይ ከመቀሌ ነግሮናል።
የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄውችን አንስቶ አስታንግድዋቸዋል። ከጥያቄዎች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት ሕውሃት በትግራይ ሕዝብ ስም አየነገደ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አጣልቶና አጋጭቶ ደም እንዲቃባ መደረጉ፤ ኢትዮጵያን የመሰለ ታሪካዊ ሃገር ታሪክ አልባና ወደብ አልባ መሆንዋ፤ የሃገሪቱ መሬትና ግዛት እየተቆረሰ ለባእዳን ሃገሮች የጅመንሻ መደረጉ፤ ይህ ድርጊት በቀደሙት መንግሥታት ተደርጎ የማያውቅ አሳፋሪና አዋራጅ ስራ በትግራይ ሕዝብ ስም መፈጸሙ ያበሳጨው ለመሆኑ በማያሻማ ሁኔታ ተነግሩዋቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ተጋብቶ ተዋልዶ አንዳልኖረ ሁሉ በክልልና በቋንቋ ለያይታችሁ አርስበርሱ ለማበላት ማንኛውንም መሰናዶና ዝግጅት በትግራይ ሕዝብ ስም እይፈጸማችሁ ይገኛል።
መልካም አስትዳደር ጨርሶ ጠፋ። እናነተው ቀማኛ አናነተው ዳኛ ሆናችሁ ሕዝቡ ሕግን አጥቶ ቶጉላላ። መንግሥት ዘራፊና ነጣቂ፤ ጉቦኛ፤ የልማት ደንቃራ፤ የሃይማኖት ጸር፤ ሕዝብ በሰላም በቤቱ ማደር አልችል አለ፤ ስራአጥነት በረከተ፤ አገርም ልትፈርስ አፋፍላይ ቆማለች በማለት እንደነገራቸውና ለነዚህ ጉዳዮች መልስ ይዛችሁ የምትመጡ ከሆነ አንቀበላችሁአለን ብሎ አንዳሰናበታቸው ተነግሩዋል። በሌሎች ክፍላተሃገራትም የገጠማቸው ተቃውሞ ከዚህ ቢበልጥ አንጅ ያላነሰ መሆኑን ስብሃትና ጓደኞች አበጥረው ያውቃሉ። ሕውሓትና ኢሃዴግ ማስተዳደር እየተሳነቸው መምጣቱም ተነግርዋል። ያአማረ አረጋዊን ሪፖርተር ጋዜጣ ርዕሰ ዓንቀጾችና ክቡር ምኒስተር በሚል የሚጽፈውን በተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ አሽሙር ነክ ጽሁፍ ላነበበ የመንግሥትን ክሽፈት መረዳት ይችላል። የሕውሓት ዋና አፈቀላጤ የኢትዮጵያ ፈርስቱ (ቤን) ከሁለት ወራት በፊት በቁጣ መልክ ያበሰረው እውነታ በቂ መስክር ነው። ከለጋሽ አገሮች የሚደርስባቸው ፖለቲካዊና የኢኮኖሚያዊ ጫናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በመካከለኛው አፍሪካ ሬፑብሊክ፤ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ያለው ቀውስ፤ በኮንጎና በናይጀሪያ ያለው የርስበርስ ግጭት፤ በሶማሊያ ያለው ትርምስ፤ በየአሃጉሩና ሃገራቱ የሚነሳው የሃይማኖት ግጭት ሕውሓት/ኢሃዴግን አያስደነግጠውም፤ አያሳስበውም የሚል ፖለቲከኛ ካለ የፖለቲካ ሃሁ ያልቆጠረ ብቻ ነው። ሌላው ቢቀር ለራሱ ህልውና ሲል ኢሃዴግ ለድርድር አይመጣም ማለት አይቻልም።
አቶ ስብሃት በማያሻም መልኩ ሃላፊነቱን ወሰድው የድርድሩን ስራ ለመጀመር መድፈራቸውና መፈለጋቸው ብቻ በራሱ ሊአስመሰግናቸው ይገባል። ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም አንዲሉ ከዚህ በፊት የተሰሩ ስሕተቶችን በማመንዥግ የሚገኝ ትሩፋት አይኖርም። መታወቅ ያለበት ሑላችንም ያንድ አገር ልጆች ነን። ችግሮችን በመወያየትና በመቻቻል ለመፍታት መሞከር የስልጣኔ ምልክት ብቻ ሳይሆን ታላቅነታችንንም የመናስመክርበት አጋጣሚ ይሆናልና እንጠቀምበት። እንግዲህ አቶ ስብሃት ኢንሴንቲቩን መውሰደ አችላለአሁ በማለታቸው ብቻ ያምበሳውን ድርሻ አንደያዙ ይወቁት። ለድርደር ዝግጁ መሆናቸውን ደግሞ ታማኒነት ያለው ሰራ በቅድሚያ በመሰራት እንዲአሳምኑን በጉጉት እንጠብቃለን። ካላደረጉት የሚአፍሩት አቶ ስብሃትና ኢሃዴግ በቻ ናቸው። አገርም በክስረት ጎዳናዋ ትቀጥላለች።
Sunday, 18 May 2014
ኢትዮጵያና ግብፅ ያቋረጡትን ድርድር እንዲጀምሩ የአሜሪካ መንግሥት ጥሪ አቀረበ
ኢትዮጵያ ለጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግብድ ግንባታ የአሜሪካ መንግሥት ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠውና ግድቡን በተመለከተ የኢትዮጵያና የግብፅ መንግሥታት ያቋረጡትን ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቀረበ፡፡
የአሜሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ባለፈው ረቡዕ የአሜሪካ መንግሥት ከሰሐራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች የሚሰጠውን ትኩረት አስመልክቶ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ከተወጣጡ ጋዜጠኞች ጋር ከአሜሪካ ሆነው በቀጥታ ቪዲዮ ኮንፈረንስ ተነጋገረው ነበር፡፡ ‹‹የአሜሪካ መንግሥት ከታላቁ የህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያና ከግብፅ መንግሥታት ጋር ትልቅ ውይይት በማካሄድ፣ ሁለቱ አገሮች ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል፤›› ሲሉ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ባለችው የታላቁ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ያለውን አቋም አስመልክቶ በተጨማሪ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በመጀመሪያ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የሚስተዋለው የቃላት ጦርነት የአሜሪካ መንግሥትን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል፡፡
ግድቡን በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት አቋም ሁለቱ መንግሥታት ወደ ንግግር መምጣት እንዳለባቸውና ተገናኝተው ሊወያዩ ይገባል፣ ያሉት ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ፣ ልዩነታቸውን ሊያስታርቁ ይገባል ሲሉ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሁለቱ ኢትዮጵያና ግብፅ መካከል የተወሰነ ድርድር እንደነበር የአሜሪካ መንግሥት የሚገነዘብ መሆኑን የገለጹት ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ፣ አሁንም ሁለቱ መንግሥታት ያቋረጡትን ድርድር በድጋሚ በመጀመር ለሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅም የሚበጅ መፍትሔ ላይ ቢደርሱ እንደሚሻል አስረድተዋል፡፡
ረዳት ሚንስትሯ ሊንዳ ቶማስ ከአፍሪካ ከተወጣጡ ጋዜጠኞች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ያደረጉት ውይይት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆን ኬሪ፣ የአፍሪካ ጉብኝት በቅርቡ በአሜሪካ በሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቅርቡ በሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ የኤርትራ፣ የዚምባቡዌ፣ የሱዳንና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪዎች እንደማይጋበዙ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን የሚስተዋለውን የእርስ በእርስ ግጭት አስመልክቶ ሁለቱ የግጭቱ ተዋናዮች የሰላም ስምምነቱን ወደ መተግበር እንዲገቡ፣ ካልሆነ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል፡፡
Friday, 16 May 2014
የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ክለላ ዛሬ በድብቅ ሊፈረም ነው!
የኢትዮ ሱዳን ዳር ድንበር በግልፅ የተከለለ እንዳልሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የሚጠቀሙት መሬት የኢትዮጵያ እንደሆነ ሲወሰድ ሱዳናውያን የሚገለገሉበትም የሱዳን ነው ተብሎ ይታሰባል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮችን ከቀያቸው እያፈናቀለ ለሱዳን ማስረከቡ ይታወቃል። ብዙ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ተፈናቅለዋል፣ የተወሰኑ ተለዋጭ መሬት ሲሰጣቸው ምንም ያላገኙም አሉ።
ድንበሩ ብዙ ዉዝግብና ተቃውሞ ያለው ሲሆን የኢህአዴግ መንግስት ከሱዳኖች ጋር በመተባበር በድብቅ ለመከለል ተስማምቷል። እንዲህ ነው የተደረገው፥ በድንበሩ አከባቢ የሚገኙ ኗሪዎች (የኢትዮጵያና የሱዳን) ድንበራቸውን አይተው ክለላውን ይፈፅማሉ፣ ይፈራረማሉ። ለሱዳን የተሰጠው መሬት ታውቋል። ሁሉም ነገር በኢህአዴግና የሱዳን መንግስት አልቋል። አሁን “የሀገር ሽማግሌዎች” እንዲፈርሙ እየተደረገ ነው። የሀገር ሽማግሌዎች እንዲፈርሙ የተፈለገበት ምክንያት የድንበር ክለላ የተከናወነው በኗሪዎች ነው እንዲባል ነው። ለሌላ ግዜም ምስክር ሁነው እንዲቀርቡ ነው።
በዚህ መሰረት በድንበሩ አከባቢ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ከተሞች ማይካድራና በረከት የተወሰኑ ሰዎች በካድሬዎች ተመርጠው “ኮሚቴ” ተሰኝተው ዛሬ ግንቦት 8, 2006 ዓም እንዲፈርሙ ወደ ሱዳን ድንበር ተጉዘዋል። እነዚህ ኮሚቴ ተብለው የተመረጡ ሰዎች ስለ ድንበሩ ይሁን አከባቢው እውቀት የሌላቸው፣ የአከባቢው ኗሪዎች ሳይሆኑ በቅርብ ግዜ ባከባቢው መሬት የተሰጣቸው ሰፈርተኞች ናቸው። ዕድሜየቸውም ከአርባ በታች ነው፣ ትምህርት የላቸውም፣ የድንበሩ ታሪክ አያውቁም፣ መሬት ስለተሰጣቸውና በካድሬዎች ስለታዘዙ ብቻ ሊፈርሙ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ የሀገር ሽማግሌዎች ሊባሉ አይችሉም። ምክንያቱም ሰፈርተኞች እንጂ ኗሪዎች አይደሉም፣ ወጣቶች ናቸው (ድንበሩ ላያውቁት ይችላሉ)፣ ትምህርት የላቸውም (የድንበር ጉዳይ ምን ያህል ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደሆነ ላይረዱ ይችላሉ) ወዘተ። ዛሬ እንዲፈርሙ የተወሰዱት በድብቅ መሆኑ ነው።
የድንበር ጉዳይና ሌሎች የሑመራ አከባቢ ኗሪዎች በማየሉ ተቃውሞ እየተቀሰቀሰ በመሆኑ ባከባቢው ተገኝቶ መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ እየሆነ ነው። የመንግስት አካላት ኗሪዎች ለሌሎች አካላት መረጃ እንዳይሰጡ እያስፈራሩ ነው። መረጃ መሰብሰብም አይፈቀድም። በዚሁ አጋጣሚ ግርማይ ወልደግዮርግስ የተባለ የድምፂ ወያነ ሬድዮ ጋዜጠኛ ባስተዳዳሪዎች ከቀረቡለት አራት ካድሬዎች ዉጭ ሌሎች ኗሪዎችን በማነጋገሩ ምክንያት ባለስልጣናት ፖሊስ ጠርተው አስረውታል። የድምፂ ወያነ ሬድዮ ጋዜጠኛ ህዝብን ሳንፈቅድልህ አገጋግረሃል ተብሎ ነው የታሰረው።
በሑመራ አከባቢ ብዙ ተደራራቢ ችግሮች አሉ። ሕገወጥ የመሬት ሽንሸና እየተደረገ ነው። ኗሪዎችን ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ስርዓቱ ያገለግላሉ ለተባሉ ሰዎች መሬት እየተሰጠ ይገኛል። ለምሳሌ አቶ ካሕሳይ ገብረሚካኤል የተባሉ ያከባቢው ኗሪ መሬታቸው ተወስዶ ለሌላ የህወሓት ካድሬ ዉሽማ ተሰጥቷል። ፍትሐዊ ያልሆነ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።
በድንበሩ ጉዳይ በድብቅ እየተፈረመ ያለው ነገር ተቀባይነት የለውም። ለሱዳን የሚሰጥ መሬት መኖር የለበትም። ተግባሩ ሕገወጥ ነው። ኢህአዴግም ለተግባሩ ይጠየቃል።
Monday, 12 May 2014
የዞን ዘጠኝና የታሳሪ ጋዜጠኞች ጠበቃ አቶ አምሃ ለቢቢኤን ራድዮ ተናገሩ
በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ታሳሪዎች ከህግ ጠበቃቸው ፡ ከቤተሰቦቻቸው ከቅርብ ወዳጆቻቸው ጋር መገናኘት እንደሚችሉ ቢደነግጉም የማእከላዊ አሳሪዎች ይህን ሊፈቅዱ አልቻሉም፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ የዞን ዘጠኝ አባላትና ጋዜጠኞች ጠበቆቻቸውን እንዲያገኙ ፍርድ ቤቱ ትዛዝ ቢያስተላልፍ የማእከላዊ ሃላፊ የሆኑት አቶ ተክላይን ጨምሮ ይህን ለማድረግ ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡” የሚሉት ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን “ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ጥብቅና መቆሜን አቆማለሁ ሲሉ” ገለጹ፡፡ የፍትህ ስርአቱም አደጋ ላይ ወድቁዋል ይላሉ ቢቢኤን ሬድዪ ከአቶ አምሃ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይከታተሉ::
Ze-Habes
Wednesday, 7 May 2014
የዞን ዘጠኝ አባላት ሕዝብ እንዳያውቅ በዝግ ችሎት ነው ጉዳያቸው የታየው ፣ እንደገና ለ10 ቀን ተቀጠሩ
ዞን ዘጠኞች እንዲሁም ጋዜጠኛ አስማማዉ፣ ተስፍዳ አለም እና ኤዴም ፍርቅ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው በዝግ ችሎት እንዲታይ ተደርጓል። ፖሊስ እንደገና ለ10 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠ ሲሆን ፣እስረኞቹ ጠበቃቸውን ለማየት እድል ያገኙት እዚያው ፍርድ ቤት ነበር።
ዝርዝር ዘገባዉ ዳዊት ሰለሞን እና ብስራት ወ/ሚካኤል እንደሚከተለው አቅርበዉታል፡
ዳዊት ሰለሞን
አስማማው፣ተስፋለም፣ኤዶም፣ዘላለም፣አጥናፍና ናትናኤል አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ሲደርሱ የጭንቅላታቸው ጭማቂ የሆኑ ፊደላትን በኮምፒዩተር ኪቦርድ የሚመቱቡባቸው ሁለት እጆቻቸው ካቴና ጠልቀውላቸው ነበር፡፡
ዲፕሎማቶች፣የውጪ አገር ጋዜጠኞች፣ቤተሰቦቻቸውና የሞያ አጋሮቻቸው ታሳሪዎቹ ነፍጥ ባነገቱ ወታደሮች ታጅበው ሲገቡ እጆቻቸውን በማውለብለብ ሰላምታ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡እስረኞቹን በፍርድ ቤት ለመወከል ስምምነት የፈጸሙት ጠበቃ አምሐ ደምበኞቻቸው ወደ ሚገኙበት ማዕከላዊ ለጥየቃ ሲመላለሱ ቢቆዩም ፈቃድ በማጣታቸው ልጆቹን የተመለከቷቸው እንደ ሁላችንም ግቢውን በረገጡበት ቅጽበት ነበር፡፡
በአንጻሩ የከሳሽ ጠበቆች(ዐቃቤ ህግ) ከተያዙበት ቅጽበት አንስተው ኬዙን ሲያጠኑና ሲያስተነትኑ መክረማቸውን መገመት አያዳግትም፡፡
ህገ መንግስቱ ለግልጽ ችሎት እውቅና ቢቸርም የጋዜጠኞቹ ጉዳይ የተሰማው በዝግ ችሎት ነው፡፡ህዝብ መረጃ የማግኘት መብት ቢኖረውም ቢያንስ ጋዜጠኞች ጉዳዩን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ፈቃድ መስጠት አለመቻሉም አሳዛኝ ነው፡፡
ጠበቃ አምሐ እንደነገሩን ከሆነ አቃቤ ህግ ክሱን ከሽብርተኝነት ጋር እንዲያያዝ አድርጓል፡፡በሁኔታው በጣም ያዘኑት ጠበቃው በቀጣዩ ቅዳሜ ማለትም ግንቦት 9/2006 ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱንም አስታውቀዋል፡፡የአስር ቀን ቀጠሮ ለፖሊስ የተፈቀደለትም‹‹ያልያዝኳቸው ግብረ አበሮቻቸውና ያልሰበሰብኳቸው ወረቀቶች አሉ››በማለቱ እንደሆነም ጠበቃው ገልጸዋል፡፡
ደምበኞቻቸውን እርሳቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ሊጠይቋቸው አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ በመናገራቸውም ዳኛው ፖሊሶቹ ታሳሪዎቹ በሰው እንዲጎበኙ እንዲያደርጉ ማዘዛቸውም ተሰምቷል፡፡
ታሳሪዎቹ ከፍርድ ቤት ሲወጡ አንድ ወጣት ፎቶ ግራፍ ሊያነሳ ይሁን የእጅ ስልኩ በማንቃጨሉ ሊያናግር ወደ ፊቱ ሲያስጠጋ ፖሊሶች ‹‹ፎቶ ልታነሳ ነው ››በማለት አንድ ጥፊ አሳርፈውበት ከጋዜጠኞቹ ጋር ወደ ማዕከላዊ ወስደውታል፡፡
ብስራት ወ/ሚካለል እንዲ ዘግቧል
ዛሬ ሚያዚያ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ከጠዋቱ 4፡00ሰዓት የነበረው ቀጠሮ ባልታወቀ ምክንያት ወደ 8፡00 ሰዓት ተዛውሮ ነበር፡፡ በ8፡00 ሰዓት በነበረው ቀጠሮም አጥናፍ ብርሃን፣ ኤዶም ካሳዬ እና ናትናኤል ፈለቀ በመጀመሪያው ዙር ወደ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፤ በ9፡00 ሰዓት ደግሞ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋዓለም ወልደየስ እና ዘለዓለም ክብረት ቀርበዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ ፖሊስ) ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቁ ለቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ጉዳዩ በዝግ ችሎት ነው በሚል ቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ጓደኛ እንዲሁም በስፍራው የነበሩ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ፣የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች ተገኝተው የነበረ ቢሆንም ችሎቱን መታደምም ሆነ መግባት በመከልከሉ ጉዳዩ በዝግ ችሎት ተከናውኗል፡፡
ቀሪዎቹ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ እና ማህት ፋንታሁን ነገ ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡00 ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡ የዛሬ ፍርድ ቤት ሌላ ለየት ያለው ክስተት የህግ ባለሙያ የሆነው ወጣት ኪያ ፀጋዬ ችሎቱን ለመታደም አራዳ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ፎቶ አንሰተሃል በሚል በማዕከላዊ ፖሊ ከነ ስልኩ ከታሳሪዎቹ ጋር ተይዞ ተወደስዷል፡፡ ኪያ ፀጋዬ ይህ እስከተፃፈ ድረስ አልተለቀቀም፡፡ የውስጥ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ ከነገ ጀምሮ ታሳሪዎቹን በታሰሩበት ማዕከላዊ እስር ቤት ሄዶ መጎብኘት እንደሚቻልም ተጠቁሟል፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)