Wednesday, 30 April 2014
የታሰሩት ጋዜጠኞችና ጦማርያን ጉዳይ እያነጋገረ ነው
-ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በነፃ እንዲለቀቁ እየጠየቁ ነው
-መንግሥት አደገኛ ወንጀል ፈጽመዋል እያለ ነው
የመብት ተሟጋቾች ነን ከሚሉ የውጭ ድርጅቶች ጋር በገንዘብና በሐሳብ በመስማማት፣ ሕዝብን ለአመፅ ለማነሳሳትና ለማተራመስ በኢንተርኔትና በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ
ቀስቃሽ መጣጥፎችን ለማሰራጨት ሲዘጋጁ ተደርሶባቸዋል በሚል፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ጋዜጠኞችና ጦማርያን (Bloggers) ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡
ሚያዝያ 25 እና 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በ48 ሰዓታት ውስጥ በዕለተ እሑድ ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በቀረቡበት ወቅት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ፖሊስ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ ድርጅቶች ጋር በገንዘብና በሐሳብ ተስማምተው ሕዝቡን ለአመፅ ለማነሳሳት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ከሚል የወንጀል የጥርጣሬ ውጪ ያለው ነገር ስለሌለ፣ ‹‹ወንጀሉ ምድነው?›› የሚል ጥያቄ ከማንሳት ጀምሮ የተለያዩ መላ ምቶችን በማንሳት የተለያዩ አካላት እየተነጋገሩበት ነው፡፡
ሲፒጄ (ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት)፣ ‹‹ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ የከፋ ከሚባሉ ዕርምጃዎች አንዱ ነው፤›› በማለት በጋዜጠኞቹና በጦማርያኑ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰደውን ዕርምጃ አውግዟል፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁም ጠይቋል፡፡
አምኒስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፣ ‹‹ይኼ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የማሰር የረዥም ጊዜ ልምድ ነው፤›› በማለት ጋዜጠኞቹንና ጦማርያኑን ማሰር ተገቢ አለመሆኑን አስታውቆ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡
ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያን መንግሥት በማውገዝ የጋዜጠኞቹንና ጦማርያኑን መታሰር የሚያነሱትን ወቀሳና ጥያቄ ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ለውጭ ሚዲያ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ በአደገኛ ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ ፖሊስ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ዙሪያ ምርምራ እያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሒዩማን ራይትስ ዎች ሚያዝያ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ የተባሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ጋር ባደረገው የስልክ ውይይት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የታሰሩትን ጋዜጠኞችና ጦማርያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ጆን ኬሪ ተጠርጣሪዎቹን እንዲፈቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊት እንዲያደርጉ በስልክ ያስተላለፈውን መልዕክት አስመልክቶ አቶ ጌታቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹መንግሥት የጋዜጠኞችን የመናገር መብት አላፈነም፣ አንዳንዶች ሙያውን ተገን በማድረግ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ሲሳተፉ ይገኛሉ፣ ይኼን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አይፈቅድም፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ትዕዛዝን አንቀበልም፤›› ብለዋል፡፡
በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞችና ጦማርያን ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በሦስት የምርመራ መዝገብ ተከፋፍለው ሲሆን፣ ቀደም ሲል በአዲስ ነገር ጋዜጣ፣ በፎርቹን ጋዜጣና በአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ላይ ይሠራ የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ነው የተባለው ጦማሪ ዘለዓለም ክብረትና የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ አንድ ላይ ናቸው፡፡
በሁለተኛው የምርምራ መዝገብ የተካተቱት የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ የነበረችው ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀና ጦማሪ አጥናፉ ብርሃኔ ሲሆኑ፣ የአየር መንገድ ሠራተኛ ነው የተባለው ጦማሪ አቤል ዋበላ፣ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉና ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን በሦስተኛው የምርምራ መዝገብ ተካተው ለሚያዝያ 29 እና 30 ቀን 2006 ዓ.ም. መቀጠራቸው ታውቋል፡፡
በምሥረታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋማ) የጋዜጠኞቹንና ጦማርያኑን መታሰር በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚገባው ጠቁሞ፣ መታሰራቸው ግን እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡ ባስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡
በአገር ውስጥ ያሉ የግል የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት መገናኛ ብዙኃን፣ ከመንግሥትና ከቅርብ ወዳጆቻቸው እንዳገኙት አድርገው በተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞችና ጦማርያን ላይ እያስተላለፉት ያለው መረጃ፣ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ ፍርድ ቤቱ በምርመራ መዝገቡ ላይ ካሰፈረው የተለየ በመሆኑ፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በቀጣይ የሚቀርበውን የምርምራ ውጤት ከመጠባበቅ ባለፈ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
Thursday, 24 April 2014
ዋና ኦዲተር ለብክነት የተጋለጡ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሒሳቦችን አጋለጠ
-ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ሒሳብ አለ
-785 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ወጪ ታይቷል
-ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ላለፉት በርካታ ዓመታት ለፓርላማ ሲያቀርበው እንደቆየው ሁሉ፣ ለብክነት የተጋለጠ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ሀብት መኖሩን ባለፈው ሚያዝያ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ለፓርላማው ይፋ አድርጓል፡፡ ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ሲሰማ የቆየው ፓርላማው ፈጣን ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የአንድ ዓመት ገደብን መስጠት መርጧል፡፡
በዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ምክንያት ሠራተኞችን ለማቆየት መቸገራቸውን የገለጹት የፌደራሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ራሳቸው ጭምር በቡድን መሪነት በተሳተፉበት የ130 የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የ2005 ዓ.ም. በጀት ኦዲት በማድረግ፣ እንዲሁም በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን የስምንት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በማሠራት፣ በአጠቃላይ የ138 መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በመተንተን የኦዲት ግኝቱን ለፓርላማ አቅርበዋል፡፡
ከቀረበው የፋይናንስ ሕጋዊነትን የተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ውስጥ አንድ ቢሊዮን 527 ሚሊዮን ብር ተሰብሳቢ ሒሳብ መኖሩን፣ ሕጋዊ ሥርዓቱን በልተከተለ መንገድ የተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች 785 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን፣ የተፈቀደው በጀት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት ደግሞ 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት መገኘቱን ይፋ አድርገዋል፡፡
ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በወቅቱ ካልተወራረደ ወይም ካልተሰበሰበ በቆየ ቁጥር የመሰብሰብና ወደ ሀብትነት የመለወጥ ዕድሉ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ፣ ኦዲት ከተደረጉት መሥሪያ ቤቶች 77 በሚሆኑት ላይ 877.1 ሚሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ሳይወራረድ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ከያዙት መካከል በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ሥልጠና ማስተባበሪያ 173.6 ሚሊዮን ብር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 149.5 ሚሊዮን ብር፣ የትምህርት ሚኒስቴር 100 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል፡፡
ዋና ኦዲተር የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰቡን ለማጣራት ባካሄደው ኦዲት 32.2 ሚሊዮን ብር ከገቢ ግብር፣ ከቀረጥና ታክስ እንዲሁም ከሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ ደንቦች መሠረት አለመሰብሰቡን አረጋግጧል፡፡
ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጀቶች አግባብ ባለው ሕግና ደንብ መሠረት የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት 326.7 ሚሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ አብዛኛው ይህ ውዝፍ ያልተሰበሰበ ገቢ የሚመለከተው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን እንደሆነ ከኦዲት ሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በጊዜያዊነት ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች የጊዜ ገደባቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የጊዜ ገደቡ በሕግ አግባብ እንዲራዘም ካልተደረገ በስተቀር በዋስትና የተያዘውን ገንዘብ የመውረስ መብት በሕግ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን በጊዜያዊነት ገብተው የመቆያ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ በድምሩ 222.5 ሚሊዮን ብር የዋስትና ገንዘብ አለመሰብሰቡን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
‹‹የሚሰበሰብ ገቢ መንግሥት ለሚያከናውናቸው የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋትና ለአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ሚና የሚኖረው በመሆኑ፣ የመንግሥት ሕግና ደንብ ተከብሮ መሠራት አለበት፤›› ሲሉ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ አሳስበዋል፡፡
ሕጋዊነት የጎደላቸው ወጪዎችን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት 785 ሚሊዮን ብር አግባብነት የጎደላቸው ወጪዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው በ25 መሥሪያ ቤቶች በወጪ ተመዝግቦ ነገር ግን የወጪውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ማስረጃ ሊቀርብበት ያልቻለ 202.6 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡
የግዥ አዋጁን እንዲሁም ደንብና መመርያን ያልተከተሉ ግዥዎችን በተመለከተ ደግሞ፣ 43 መሥሪያ ቤቶች 165.9 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ወጪ አድርገዋል ብለዋል፡፡ ሌሎች 41 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 76 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ክፍያ መፈጸማቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
ሒሳቦች በወጪነት የሚመዘገቡት የሚፈለገው አገልግሎት መገኘቱን ወይም የሚፈለገው ንብረት በአግባቡ በእጅ መግባቱ ሲረጋገጥ ቢሆንም፣ 13 መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቱን ወይም ንብረቱን ሙሉ በሙሉ ሳያገኙ የከፈሉትን የ234.8 ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያ በወጪ መዝገብ ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በመሆኑም የተፈለገው አገልግሎት ወይም ንብረት ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ በተሰብሳቢ መያዝ ይኖርበታል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በ104 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ለተለያዩ ግዥዎች አራት ሚሊዮን 471 ሺሕ ብር ያላግባብ በብልጫ መከፈሉን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም በአሥር መሥሪያ ቤቶች የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልቀረበለት 22.6 ሚሊዮን ብር ወጪ መኖሩን፣ በሌሎች ሰባት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር ቀረጥ የተከፈለባቸው ንብረቶች ገቢ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ቀረጥ ተከፍሎባቸው ንብረቶቹ ገቢ ለመሆናቸው ለማረጋገጥ ካልተቻለባቸው መሥሪያ ቤቶች ትልቁን ድርሻ የያዘው፣ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ሲሆን፣ በቀጣይነት ደግሞ ጤና ጥበቃና ትምህርት ሚኒስቴር ተጠቅሰዋል፡፡
በ23 መሥሪያ ቤቶች የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ 90.9 ሚሊዮን ብር መኖሩን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የፌደራል መንግሥት ግዥ አፈጻጸም መመርያ በግንባታ ቦታ ላይ ላሉ ዕቃዎች፣ ወይም ግንባታ ላይ ላልዋሉ ክፍያ መፈጸምን የሚከለክል ቢሆንም፣ 11 መሥሪያ ቤቶች ይህንን በመጣስ 168.6 ሚሊዮን ብር መክፍላቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ መንግሥት የግንባታ ዕቃዎችን በብድር ሲያገኝ የተገኘው ቁስ መጠን ተሰልቶ ከግንባታ ወጪ ላይ መቀነስ የሚገባው ቢሆንም፣ አራት መሥሪያ ቤቶች ግን 18.3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ በብድር የተገኙ የግንባታ ዕቃዎች ወጪን ሳይቀንሱና ለመንግሥት ካዝና ሳያስገቡ በኦዲቱ ተገኝተዋል፡፡
የተፈቀደላቸውን በጀት በትክክል ለሥራ አውለዋል ወይ የሚለውን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት ደግሞ፣ በ96 መሥሪያ ቤቶች 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል፡፡ ይህ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት የነበረ ቢሆንም፣ የፓርላማው አባላት በቁጭትና በእልህ እንዳለፈው ዓመት ሲናገሩ አልተስተዋሉም፡፡
ብቸኛው የፓርላማ የግል ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የኦዲት ሪፖርቱን አስመልክተው፣ ‹‹በዚህ አገር ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም የሚሉ ባለሥልጣናት ያሉ ይመስለኛል፡፡ እርስዎ እንደዚያ ያስባሉ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ዋና ኦዲተሩን አቶ ገመቹ ዱቢሶን ጠይቀዋል፡፡
አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ምላሽ፣ እንዲዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ፣ ነገር ግን ችግር መኖሩን እያወቁ የማያስተካክሉ ኃላፊዎች መኖራቸውን፣ አንዳንድ ጊዜ በሒሳብ ባሙያዎች የሚታለሉ ኃላፊዎች እንዳሉ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
መደረግ የሚገባውን በተመለከተ በዶ/ር አሸብር ለተነሳው ጥያቄ ዋና ኦዲተሩ የሰጡት ምላሽ በዋና ኦዲተርና በአፈ ጉባዔው መካከል በተደረገ ስምምነት በ2006 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት ላይ የሚገኙ የኦዲት ግኝቶች እስካሁን በነበረው ግዝፈት የሚቀጥሉ ወይም የማይሻሻሉ ከሆነ፣ ሕጋዊ ቅጣት በመሥሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎች ላይ ለመውሰድ ስምምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፓርላማው ቋሚ ከኮሚቴዎች የሚከታተሏቸውን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በይበልጥ መጠየቅ እንደሚገባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. የ2006 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ለማቅረብ በፓርላማው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ጥያቄ ይቀርብላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Tuesday, 22 April 2014
እውቅና የተሰጠው የሚያዚያ 26ቱ የአንድነት ሰልፍ በደህንነቶች ትእዛዝ እውቅና ተነፈገ
ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና እንደሚጠቁመው፣ የአንድነት ፓርቲ ሚያዚያ 19 ሰልፍ ለማድረግ ቢጠይቅም፣ የፖሊስ አዛዞች በዚያን ቀን በቂ ጥበቃ ማዘጋጀት አንችልም በማለታቸው፣ አስተዳደሩ ሚያዚያ 26 ቀን እንዲደረግ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ ለሚያዚያ 26 የእውቅና ደብዳቤ ለመዉሰድ ወደ አስተዳደሩ ጽ/ቤት ያመሩት የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች፣ የእውቅና ደብዳቤ ሳይቀበሉ መመለሳቸውን ያነጋገርናቸው የአንድነት አመራር አባል ገለጹ።
የአስተዳደሩ ሃላፊዎች፣ ከደህንነት ጽ/ቤት ለአንድነት ሰልፍ እውቅና እንዳይሰጡ በቀጥታ መታዘዛቸዉን የገለጹት የአንድነት አመራር ፣ አዲስ አበባ በከንቲባው ሳይሆን፣ የአዲስ ሕዝብ ባልመረጣቸው ከበስተጀርባ ሆነው በሚፈልጡና በሚቆርጡ ጥቂቶች መዳፍ ስር የወደቀችና በአምባገነኖች የምትገዛ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።
አንድነት ፣ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ፣ ሰልፍ ለማድረግ በአገዛዙ እውቅና ያልተሰጠበት የሚያዚያ 26 ቀኑ፣ አራተኛው ቀን ሲሆን፣ ከፋሲካ እሁድ ዉጭ ባሉ ሶስት እሁዶች ፣ መጋቢት 28፣ ሚያዚያ 5 እና ሚይዚያ 19 ቀንም ሰልፍ ለማድረግ ተጠይቆ በደህንነቶች ትእዛዝ እውቅና አለመሰጠቱ ይታወቃል።
ከሰልፍ ጋር በተገናኘም የአዲስ አበባ አስተዳደር ሚያዚያ 19 ቀን ሰልፍ ለማድረግ አንድነት ፓርቲ ጠይቆ እውቅና አልሰጥም ቢልም፣ ለአንድነት በተከለከለበት ቀን ለሰማያዊ ፓርቲ እውቅና እንዲሰጥ የደህንነት ሃላፊዎች መመሪያ መስጠታቸውን፣ በአዲስ አበባ ያሉ ምንጮቻችንን በመግለጽ መዘገባችን ይታወቃል።
በአንድነት ፓርቲ ላይ እየተደረገ ያለው ሕግ ወጥ እርምጃ፣ ከአስተዳደሩ ዉጭ ያሉ የደህንነት ሃላፊዎች፣ በቀጥታ የአስተዳደሩ የሰማያዊ ሰልፍ ፍቃድ ኦፊሰር የሆኑትን፣ አቶ ማርቆስን ፣ በማዘዝ እየፈጸሙት ያለ አሳዛኝ ተግባር እንደሆነ የገለጹት የአንድነት አመራር፣ ከከንቲባው ጽ/ቤት ሃላፊዎች ጋር የፓርቲዉ ከፍተኛ አመራሮች ችግሮችን ለመፍታት በስፋት እንደተነጋገሩ ገልጸዋል። አንድነት ሚያዚያ 19 ቀን ጠይቆ ፣ «ሌላ ዝግጅት አለ። በቂ ጥበቃ የለም» በሚል ሚያዚያ 26 ማድረግ እንደሚቻል እንደተነገራቸው የገለጹት የአንድነት አመራር፣ አሁን ሌሎች ድርጅቶች በሚያዚያ 19 ሰልፍ እንዲጠሩ እውቅና ለመስጠት መዘጋጀቱ፣ በቂ ጥበቃ ከየት ሊገኝ ቢችል ነው በሚል የአስተዳደሩን ሃላፊዎች ጠይቀዋል።
የአስተዳደሩ ሃላፊዎች ጉዳዩን ተከታትለው፣ ነገ ሚያዚያ 15 ቀን እንደሚያሳውቋቸው መግለጻቸዉን፣ የሚናገሩት የአንድነት አመራር አባል፣ አስተዳደሩ መጀመሪያ ለጠየቀዉ ፓርቲ፣ አስፈላጊዉን ቅድሚያ እንደሚሰጥና ሕግን አክብሮ በሕግ የተደነገገለትን ሃላፊነት እንደሚወጣ፣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በሃያ ሶስቱም የአዲስ አበባ ወረዳዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላትና ደጋፊዎች እንዳላቸው የገለጹት የአመራር አባሉ፣ አስተዳደር እውቅና ሰጠ አልሰጠም፣ በቅርብ ቀናት ዉስጥ ለሚያዚያ 19 ይሁን ሚያዚያ 26 ቅስቀሳ እንደሚጀምር አሳወቀዋል።
አገዛዙ የዜጎችን መብት ማፈን እንደማይችል ያስረዱት አመራር አባሉ፣ አንድነት በሰለጠነና በመግባባት ፖለቲካ ቢያምንም፣ ሕግ መንግስቱ የሚደነግግለት መብት ላይ እንደማይደራደር አረጋግጠዋል። «ሰልፉ ይደረጋል። ጥያቄዉ ፖሊስ ሕዝብን ይጠብቃል ወይንስ ከሕዝብ ጋር ይጋጫል? የሚለው ነው» ሲሉ ነበር የአንድነት ቁርጠኝነት ለማሳየት የሞከሩት።
ፓርቲዉ በዚህ ረገድ፣ እየትሰራ ያለዉን ደባ ለማጋለጥና ሕዝብ አጥርቶ እንዲያወቀው ለማድረግ፣ በመረጃ ላይ የተደገፈ መግለጫ እንደሚሰጥም ለማወቅ ችለናል።
የአዲስ አበባ አስተዳደርና አንድነት ከመግባባት ደረጃ ደርሰው፥ የታቀደው ሰልፍ ሕጉን በጠበቀ መልኩ ሚያዚያ 19 ይሁን ሚያዚያ 26 ይደረግ እንደሆነ፣ ያ ካልሆነ ደግሞ የአንድነት ፓርቲ ዉሳኔ ምን እንደሚሆን ተከታትለን ለማቅረብ እንሞክራለን።
Sunday, 13 April 2014
ደሴዎች ሆይ ! ቁጭታችሁ ቁጭታችን፤ ብሶታችሁ ብሶታችን ነው።
በደሴ ሚሊየኖች የመሬት ባለቤት እንሁን ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጩኽዋል።መሬት ክብር ነው። መሬት ሃብት ነው። መሬት ማንነትም ነው። ይህ ክብር፤ ይህ ሃብት፤ ይህ ማንነት ከህዝቡ ላይ ተወስዷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የመሬቱ ባለቤት ህወሃት-ኢሕአዴግ ነው። ይሄ ቡድን መሬቱን ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም “የእኔ ንብረት ነው” የሚል አስተሳሰብ አሳድሯል። በዚህ አስተሳሰቡም የወደደውን ሲተክል፤ የጠላውን ሲነቅል ብዙ ዓመት ኑሯል። ከዝያም “ህዝቡ ተኛ ብንለው ይተኛል፤ ተነስ ስንለውም ይነሳል” እያለም ይሳለቃል። እውነት ነው መሬት አልባ የሆነ ዜጋ ተኛ ሲባል ከመተኛት፤ ተነስ ሲባልም ከመነሳት ሌላ ምን የተሻለ አማራጭ አለው? ለዚህ አማራጭ ላጣ ህዝብ አማራጭ ይኖረው ዘንድ የምትተጉ ወገኖችን ከልብ እናደንቃለን።
የደሴውን ሰልፍ ያዘጋጃችሁ ዜጎች ተስፋ አለመቁረጣችሁ ይደነቃል። ከፍ አድርጋችሁ የጮኻችሁት ጩኽት በኢትዮጵያ ውስጥ ከዳር አሰክ ዳር ተስተጋብቷል። ይሄን ድምፅ ያልሰማው ህወሃት-ኢሕአዴግ ብቻ ነው። ይሄ ቡድን “ማን አባቱ ይጠይቀኛል” የሚል ከንቱ እብሪት ዓይኖቹ እንዳያዩ፤ ጆሮዎቹም እንዳይሰሙ ስላገዱት የሰልፉን ድምፅ አላየሁምም አልሰማሁምም ብሏል። ህወሃት ማስተዋል የሚችል ቢሆን ኑሮ ይሄን ድምፅ አድምጦ መልስ ቢሰጥ እንደሚበጀው ያውቅ ነበር። ግን ምን ያደርጋል “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይበቀል” የምትለዋን እንስሳ መምሰልን የመረጠ ቡድን በመሆኑ ይሄን መሰሉን ድምፅ ሲሰማ “እኔ የኢያሪኮ ግንብ አይደለሁም በጩኸት የምናደው ” እያለ ይሳለቃል።እንዲያውም “የእኔን ፖሊስ ማስቀየር የሚቻለው በመቃብሬ ላይ ነው” እያለ እንደሚፎክርም መታወቅ አለበት።
ህወሃት-ኢሕአዴግ መንግስት ሊሸከመው የሚገባውን አገራዊ ኃላፊነት ለመሸከም ብቃት ያለው ቡድን አይደለም። ይሄ ቡድን የመንግስት ቅርፅና መልክ የለውም። የዚህ ቡድን መልኩና ቅርፁ “የመርሲነሪስ” መልክና ቅርፅ ነው። ይህን መልክና ቅርፅ የያዘን ቡድን ነጭ ሪባን እያውለበለብኩ ከያዘው የጥፋት ጎዳና እመልሰዋለሁ ብሎ ማመን ለእኛ የሚቻል አይደለም። የማይቻለውን ይቻላል ብላችሁ የተነሳችሁ ወገኖች ትዕግስታችሁን እናደንቃለን። ህወሃት ከሆነው ወይም ከተናገረው ውጪ ሌላ ስብዕና የለውም። የያዝኩት የጥፋት መንገድ የሚቀየረው በመቃብሬ ላይ ነው፤ ፖሊሲየን ለማስቀየር የሚፈልግ ካለም በሊማሊሞ በኩል ብቅ ይበል ማለቱ እውነት ነው። እኛ ይሄን እውነት አምነናል። የእናንተን ትጋትና ት ዕግስት ግን ከልብ እናደንቃለን።
ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ የዜጎች የማይገሰሰ መብት ነበር። ህወሃቶች ፅፈው ለህዝቡ የሰጡት ህግ መንግስትም ይሄን ይመስከራል። ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ እንጂ ፈቃድ መጠየቅ አያሰፈልግም የሚል ህግም አለ። ህወሃት-ኢሕአዴጎች ግን በዚህ ቀን አልፈቀድንም፤ በዚህ አካባቢ ከልክለናል እያሉ ራሳቸው የሠሩትን ህግ ከአፈር ይቀላቅሉታል። በዚህም የዜጎችን የመሰብሰብ መብት ይጥሳሉ። ጣሊያኖች በአገራችን በቆዩባት በዚያች አጭር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን በዚህ በኩል አትለፉ፤ በዚያ በታች በኩል ሂዱ እያሉ ያንገላቱ ነበር። ህወሃት-ኢሕአዴጎችም ቀኝ ገዢዎች የሚፈፅሙትን ዓይነት አድሎ በዜጎች ላይ እየፈፀሙ ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊያን በመስቀል አደባባይ መስበስብ ሲከለከሉ፤ ህወሃት-ኢሕአዴጋዊያን ግን በመስቀል አደባባይ ከበሯቸውን እየደለቁ በደስታ ይጨፍሩበታል ማንስ ይከለክለናል እያሉ ያዜሙበታል።
እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱን ክፉና ዘረኛ ቡድንን በሰላም አደብ ለማስገዛት የምትጥሩ ወገኖች በርቱ።ባለፈው በባህር ዳር የተደረገው የተቃውሞ ሠልፍ በግሩም ሁኔታ ተጠናቋል። ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር እንደሚሻልም አስተምሯል። ከሠልፉ በኋላ መንግስት ነኝ ከሚለው አካል የተሰጠ መልስ የለም።ዓለምነህ መኮንን ግን እሰከ አሁን በወንበሩ ላይ አለ። አሁን ደግሞ በደሴ “ የሚሊየኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪ ቃል ሠልፍ ተደርጓል። ይሄም በግሩም ሁኔታ ተጠናቋል። አሁንም መልስ የሚሰጥ አካል ብቅ አለማለት ብቻ ሳይሆን ሠልፉን የሰማም አይመስልም። ነገ ደግሞ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢ ሌላ ሰልፍ ይደረጋል።ይሄም ግሩም ሃሳብ ነው።ከሰልፉ በኋላ የህዝቡን ሮሮ ሰምቶ መልስ የሚሰጥ አካል ይኖር እንደሆነ አብረን እናያለን።
ኢትዮጵያዊያን መከራችን ቡዙ ነው።ዋነኛው የመከራችን ምንጭ ግን ህወሃት-ኢሕአዴግ ነው። በአሁን ሠዓት በኢትዮጵያችን ከተጋረጠው ችጋር በላይ ችግር የሚሆንብን ህወሃት ነው። ይሄ ዘረኛ ቡድን የመከላከያ ኃይሉን፤ የደህንነት ተቋሙን፤ የንግድ አምባዎችን ያቆመበት መሠረት ከሶሪያው አሳድ አገዛዝ ጋር አንድ ነው። ዛሬ ሶሪያ የገባችበት መከራ በቀላሉ የሚቋጭ አልሆነም። ምክንያቱም የስልጣኑን እርከን የተቆጣጠሩት ቡድኖች መሠረታቸውን ያቆሙት በጎሳ ላይ በመሆኑ ነው። የህወሃት መሠረቱ ጎሳ ነው። በጎሳ ተደራጅቶ የሌላውን ጎሳ ሲያንገላታ እነሆ ሁለት አሥርተ ዓመታት ሞላው። በጎሳ ተደራጅቶ ሌላውን ሲዘርፍ ብዙ ዓመት ተቆጠረ። ሌላው ጦሙን ሲያድር እርሱ ብቻ በልቶ የሚያድር ሆነ። የሌላው ልጅ በበርሃ ቀልጦ ሲቀር፤ ገሚሱ የአዞ እራት ሲሆን የእርሱ ልጆች ግን በአውሮፓና በአሜሪካን ለትምህርት የሚላኩ ሆኑ። በህወሃት የሚፈፀመውን አድልዎ በቃል ለመግለፅ ከምንችለው በላይ ነው። እንዲህ መሠረቱን በአድልዎና በጎሳ ላይ ያቆመ ቡድንን ከተቆናጠጠበት የዝሪፊያ ወንበር ላይ ለማውረድ የሚጠይቀው መሥዋዕትነት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። እስከ አሁንም ብዙ መሥዋዕትነት ተከፍሏል። ገና ወደፊትም ብዙ መሥዋዕትነት ይጠይቃል። ለዚህ ራስን በቅጡ አደራጅቶና ተባብሮ መታገል ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ሁኗል።
የመንግስት ሳይሆን የወሮ በላ መልክና ቅርፅ ካለው ቡድን ፊለፊት ቆማችሁ በየቦታው የምታሰሙት የተቃውሞ ድምፅ መልካም ነው።ብዙ መሥዋዕትነትም እያሰከፈላችሁ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይሄ የምትከፍሉት መሥዋዕትነት በከንቱ እንዳይሆን ግን አጥብቆ ማሰብ ይገባል። እስከ አሁን ብዙ ጥያቄዎች ተነስተዋል። የአማራን ህዝብ ያዋረደው ግለሰብ ለፍርድ ይቅረብ የሚል ድምፅ በባህር ዳር ተስተጋብቷል። የአማራን ህዝብ የሰደበው ግለሰብ ግን እኔ አልተሳደብኩም፤ ተቃዋሚዎች ቆርጠው ቀጥለው ያቀረቡት ነው እያለ ይሳለቃል። በሌላ በኩል ደግሞ በከተማዋ ውስጥ ያሉትን ኮምፒውተሮች ለቃቅሞ መረጃውን የላከውን ዜጋ ፍለጋ ሌሎች ዜጎችን እያሰቃየ ይገኛል። ይህን መሰሉን ንቀት ልንሸከም አይገባንም። ህወሃት-ኢሕ አዴጎች ለህዝብ ጥያቄ መልስ እንዳይሰጡ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ እንደገና መጠየቅ ይኖርበታል። የሚመራውን ህዝብ የሰደበ ግለሰብ ለፍርድ መቅረቡ አግባብ ነው። ይሄ ስደብ ግን የግለሰብ አፍ ወለምታ ሳይሆን የድርጅቱ አቋም ነው። ድርጅቱ ለፍርድ ሊቀርብ አይችልም። አዎን ኢሕኢደግ አይከሰሰም፤ ሰማይም አይታረስም የሚል ተረት አላቸው። እንግዲህ ምን ይሻላል? ይሄ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን ትክክለኛውን መልስ እስኪሰጥ ድረስ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ትክክለኛዋ መልስ ደግሞ ሰዳቢው ለፍርድ መቅረብ ብቻ ሳይሆን ፍትህ፤ እኩልነት እና ነፃነት በዚያች አገር ነግሰው መታየት ነው።
የተከበራችሁ ያገራችን ዜጎች አገራችን ያለችበት ችግር ከእሪታ በላይ ነው። እሪ ብንልም የሚሰማ መንግስት የለንም። የሚሰማ መንግስት የለም ተብሎ ዝም ማለት ግን ትክክለኛ ምርጫ አይደለም። በሚቻለው መንገድ ሁሉ በጫንቃችን ላይ ቁጢጢ ያሉ ወሮበላዎችን ማስወገድ ግድ ነው። ህወሃት-ኢህአዴጎች ሳይፈለጉ በዜጎች ጫንቃ ላይ ቁጢጢ ብለው ሃያ ዓመት አለፋቸው።”ሳንፈልጋቸው ሃያ ዓመታቸው” የሚባል ቅኔ ቢዘረፍላቸውም አልገባቸውም። የእነርሱ ምኞት ሌላውን ሁሉ እንደ ሰም አቅልጦ፤ እንደብረት ቀጥቅጦ መግዛት ነው። ሁል ግዜ እነርሱ ከላይ፤ ሌላው ሁሉ ከታች እነርሱን ተሸክሞ እንዲኖር ብርቱ ምኞት አላቸው። ይሄንንም እውን ለማድረግ ራሳቸውን ህግ አድርገው ቀርፀዋል። የአገሪቷም ፍትህ በእነርሱ ስሜት እየተወሰነ ዜጎችን ለማጥቂያነት ውሏል። የፍትሁን ሥርዓት አፈር ከድሜ ካስገቡት በኋላ ሰለዴሞክራሲ ሊነግሩን ሲነሱ የዓይናቸው ሽፋሽፍት እንኳ አይርገበገብም። እነዚህ ቡድኖች ጭካኔን ከጀግንነት መለየት የማይችሉ ፍፁም ርህራሄ የሌላቸው ናቸው። ይሄን ቡድን ነጭ ሪባን እያውለበለቡ ከተቆናጠጡበት ወንበር የማውረዱ ትግል ቢሳካ ለሁላችንም እፎይታ ይሆን ነበር።እኛ ግን ህወሃት-ኢሕአዴግ በሠላማዊ መንገድ ስልጣኑን ለህዝብ ያስረክባል የሚል እምነት የለንም።
የተከበራችሁ ወገኖቻችን !
እንግዲህ እናንተም በያዛችሁት መንገድ እንዲሳካላችሁ እንመኛለን። እኛም በአገራችን ፍትህ፤ እኩልነት እና ሙሉ ነፃነት እስከሚሰፍን ድረስ የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን። የእኛም ሆነ የእናንተ መዳረሻ ግቡ አንድና አንድ ነው። አገራችን ከዘረኞችና ከዘራፊዎች ፀድታ፤ ፍትህ እኩልነትና ነፃነት ነግሶ፤ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ እና ሠላም ሠፍኖ ማየት ነው ግባችን።እኛ በሊማሊሞ በኩል ብቅ በሉ ያሉትን ሰምተን በዚያው አያቶቻችን ባለፉበት የነፃነት መንገድ ልንጓዝ ስንቃችንን እያሰናዳን ነው። የአያቶቻችንን ጋሻና ጦር ከተሰቀለበት አውርደን እየወለወልን ነው። ከእንግዲህ ወዲያ ከህወሃት-ኢሕአዴግ የምንጠብቀው ምንም በጎ ነገር የለም። እነርሱ ተጭነውን፤ እኛ ተሸክመናቸው ለዘላለም አንኖርም። እነርሱ ሰጪ እኛ ተቀባይ፤ እነርሱ ፈቃድ ሰጪ እነርሱ ፈቃድ ከልካይ ሆነን ለዘላለም አንኖርም። ለነፃነት የሚከፈለውን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ሳናቅማማ ተነስተናል።
በመጨረሻም ለህወሃቶች እንዲህ እንላችኋለን “ነፃነታችንን ስጡን ወይም ነፍሳችንን እንኳት” አበቃን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
Friday, 11 April 2014
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የእሪታ ቀን ሰልፉን ከሶስት ሳምንታት በኋላ ለማድረግ ወሰነ !
መጋቢት 28 ቀን ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀዉ የአንድነት የእሪታ ቀን ሰልፉ ፣ «ሰልፍ እንዲደረግ በታሰበበት ቀን፣ ሌሎች ዝግጅቶች ስላሉ በቂ ጥበቃ ልናሰማራ አንችልም» በሚል እውቅና ባለመስጠቱ ለሚያዚያ 5 ቀን መተላለፉ ይታወቃል።
የሚያዚያ አምስቱን ሰልፍ በተመለከተ ምላሽ የሰጠው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በሚያዚያ 5 ቀን ፣ ሩጫ ስለሚኖር ሰልፉ ለቅዳሜ ሚያዚይ 4 ቀን እንዲደረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአንድነት ፓርቲ የላከ ሲሆን፣ የሚያዚያ አራቱን ቀን ፣ ቅዳሜ በመሆኑና ግማሽ ቀን ሥራ የሚኖራቸው በርካታ ዜጎችን ስለሚኖሩ፣ አስተዳደሩ በጠየቀው ቀን ሰልፉን ለማድረግ ፍቃደኛ እንዳልሆነም የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች በጉዳዩ ላይ መክረዉበት ፣ የሚቀጥሉት ሁለት እሁዶች የባህል ቀናት እንደመሆናቸው፣ ከሶስት ሳምንታት በኋላ ሰልፉን ለማድረግ ማሰባቸውን ያነጋገርናቸው ከፍተኛ የአንድነት አመራር አባል ገልጸዉልናል።
ያንን በተመለከተ አስፈላጊዉን የማሳወቅ ደብዳቤ ለአስተዳደሩ የሚያስገቡ ሲሆን፣ በዚህ ሂደት፣ የተለያዩ ሩጫዎችን ለማስተናገድ ሲባል፣ መንገዶች ሲዘጉ፣ የትራፊክ መጨናነቅና የልማት ሥራ መደናቀፍ ሲፈጠር፣ ያላሳሰበው፣ የአዲስ አበባ አስተዳደሩ፣ ሕዝቡ ሕግ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ድምጹን ለማሰማት ሲዘጋጅ ይጨናነቃል፣ «የልማቱ ሥራ ይደናቀፋል፣ የትራፊክ መጨናነቅ ይኖራል» እያለ እውቅና አለመስጠቱ አሳዛኝ እንደሆነ የሚናገሩት የአመራር አባሉ ፣ «የኛን ሞራል ሞራል ለማዳከም የሚያደርጉት አሳዛኝ እንቅስቃሴ፣ ዉጤት እንዳመጣላቸው፣ ይልቅስ የበለጠ በቁርጠኝነት እንድንነሳ የሚያደርግ መሆኑን አውቀው፣ ከሶስት ሳምንት በኋላ አስፈላጊዉን ትብብር ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለኝ» ሲሉ በፓርቲያቸው ዘንድ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
የአንድነት ፓርቲ መጋቢት 28 ቀን በደሴ ከተማ እጅግ ታልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ይታወቃል። ፓርቲዉ ከደሴና ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዋሳ፣ ድረዳዋ፣ አዳማ በመሳሰሉት ወደ 14 በሚጠጉ ከተሞች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሆነም በስፋት ተዘግቧል።
Saturday, 5 April 2014
ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ለማስመለስ የኢህአዴግ ልኡካን በጄኔቫ
ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በአቶ አስመላሽ ወልደ-ስላሴ የተመራ ከፍተኛ የኢህአዴግ ልኡካን ቡድን ጄኔቭ፣ ስዊዘርላንድ ከርሞ ባለፈው ሳምንት ተመልሷል።
በፓርላማው የህግ እና የአስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደ-ስላሴ የተመራው ይህ ቡድን ከሜይ 13፣ 2014 ጀምሮ የስዊዘርላንድ መንግስት አካላት ጋር በሃይለመድህን ጉዳይ ላይ ለቀናት ተወያይቷል። ስዊዘርላንድ ረዳት ፓይለቱን አሳልፋ እንድትሰጥም ቡድኑ ብዙ ሙከራ አድርጎ እንደነበርና ሙካራው ሁሉ ሳይሳካ መቅረቱንም ለማወቅ ችለናል።
ቡድኑ የስዊስ ፌዴሬሽን የህግ አካላትን ለማሳመን ካቀረበው ምክንያት ዋነኛው፣ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ የአእምሮ በሽተኛ መሆኑን እና ይህንንም ከራሱ ቤተሰብ አባላት እንዳረጋገጡላቸው ገልጸዋል። የስዊዝ መንግስት ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። ለዚህም የሰጠው ዋነኛ ምክንያት፤ የሞት ፍርድን ተግባራዊ ለሚያደርግ መንግስት ማንንም አሳልፌ አልሰጥም የሚል ሲሆን ይህ ባይሆንም፣ በስዊዘርላንድ እና በኢትዮጵያ መሃል ተጠርጣሪ እስረኛን የማስመለስ ውል የለም ብለዋል።
በተያያዘ ዜና ወንድሙ ዶ/ር እንዳላማው አበራ እና በጀርመን የምትኖር እህቱ ሃይማኖት አበራ ጄኔቭ ድረስ በመምጣት የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ከሚገኝበት እስር ቤት ጎብኝተውታል። የስዊስ ጠበቆችም የፓይለቱ መብት እንዲከበር አጥብቀው እየሰሩ ይገኛሉ። መገናኛ ብዙሃን ላይ ሲደሰኩሩ የነበሩ አንዳንድ የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያዎች እዚህ ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ ሲጠየቁ አሳፋሪ ምላሽ መስጠታቸውንም ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉት ኢትዮጵያውያን ለመረዳት ችለናል።
ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ባለፈው የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ቦይንግ 767 አግቶ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ላይ በማሳረፍ እዚያው የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁ ይታወሳል። የአለም ዜና ርዕስ ሁሉ ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ ልዩ ክስተት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ሁኔታና የአስተዳደር በደል አደባባይ በማውጣቱ የገዢው ፓርቲ አባላትን እጅግ እንዳበሳጨ ይነገራል።
አንዳንድ መገናኘ ብዙሃን እንደገለጹት የአጎቱ ድንገተና ህልፈት ርዳት ፓይለቱን አስቆጥቶት ነበር። የሃይለመድህን አበራ አጎት፤ ዶ/ር እምሩ ሥዩም ህይወት በድንገት ማለፍ ለብዙዎች ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ዶ/ር እምሩ ሥዩም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ።
በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቱ ፓይለት ሃይለመድህን አበራን መደገፋቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን በረዳት ፓይለቱ ስም የተከፈቱ ድረ-ገጾች እና የፌስቡክ መድረኮች ላይ ሰፊ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የስዊዝ ቴሌቭዥን በረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ዙርያ አንድ ዘጋቢ ፊልም የሰራ ሲሆን ይህ ዘገባ ለትንሽ ግዜ እንዲዘገይ ተደርጓል። ዘጋቢ ፊልሙ አየር ላይ ያልዋለበት ምክንያት የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ጠበቆች እንዲዘገይ በመጠየቃቸው ነው ሲሉ ጉዳዩን የሚከታተሉት ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል::
ዘ-ሐበሻ
Subscribe to:
Posts (Atom)